በከተማው እየተከናወኑ ያሉ የትምህርት ጥራትን የማስጠበቅ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በከተማው እየተከናወኑ ያሉ የትምህርት ጥራትን የማስጠበቅ ተግባራት ይጠናከራሉ
ገንዳውኃ፤ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ)፦ በገንዳውኃ ከተማ አስተዳደር እየተከናወነ ያለው የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻልና የትምህርት ጥራትን የማስጠበቅ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።
በገንዳ ውኃ ከተማ አስተዳደር የ2019 ዓ.ም የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ዛሬ ተጀምሯል።
የአስተዳደሩ ተወካይ ከንቲባ አቶ አዳነ ሀሰን በፕሮግራሙ ማስጀመሪያ ላይ እንደገለጹት፤ በገንዳውኃ ከተማ አስተዳደር እየተከናወነ ያለው የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻልና የትምህርት ጥራትን የማስጠበቅ ተግባራት ይጠናከራሉ።
ከነዚህም ውስጥ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር አንዱ መሆኑን ገልፀው ይህም የከተማ አስተዳደሩ በሚመድበው በጀት፣ በባለሃብቶችና በህብረተሰቡ ትብብር ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል።
የምገባ ፕሮግራሙ የተማሪዎችን የመማር ፍላጎትና አቀባበል ማሳደግ፣ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማድረግ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ የሚያስችል ውጤት ማስገኘቱን ገልጸዋል።
የተገኘውን ጥቅም ለማሳደግም የዘንድሮውን የምገባ ፕሮግራም ፈጥኖ በማስጀመር ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መሰራቱን አስረድተዋል።
ከምገባ ፕሮግራሙ በተጨማሪ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል፣ ግቢን በማስዋብና ሌሎች ተግባራትን በማከናወን የትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በየነ አዳነ በበኩላቸው፤ በትምህርት ዘመኑ በ3 ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ከሁለት ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የምገባ ፕሮግራም እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት የተካሄደው የምገባ ፕሮግራም ተማሪዎች ትምህርታቸውን በንቃት እንዲከታተሉና የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ማስቻሉን የጠቆሙት ደግሞ የገንዳ ውኃ ቁጥር 1 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሀብቱ ተስፋ ናቸው።