የኬንያ የጀግንነት እና የመስዋዕትነት ታሪክ ከኢትዮጵያ የአድዋ ታሪክ ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል - ኢዜአ አማርኛ
የኬንያ የጀግንነት እና የመስዋዕትነት ታሪክ ከኢትዮጵያ የአድዋ ታሪክ ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ)፦የኬንያ የጀግንነት እና የመስዋዕትነት ታሪክ፤ ከሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለመከላከል በአንድነት ከቆሙበት ከኢትዮጵያ የአድዋ ታሪክ ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፦ዛሬ በኤልዶሬት፣ ኬንያ በተከበረው የማሹጃ ቀን (የጀግኖች ቀን) ብሔራዊ ክብረ በዓል ላይ በመገኘትና ንግግር በማድረግ፤ ለሀገራቸው ነጻነት ለታገሉና ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር ታላቅ መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች ያለኝን ታላቅ ክብር ገልጫለሁ ብለዋል።
ለጀግንነታቸውና ትተውት ላለፉት ዐሻራ የላቀ ክብር አለኝ ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የኬንያ የጀግንነት እና የመስዋዕትነት ታሪክ፤ ከሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለመከላከል በአንድነት ከቆሙበት ከኢትዮጵያ የአድዋ ታሪክ ጋር በእጅጉ እንደሚመሳሰልም ጠቁመዋል።
እነዚህ የጋራ ታሪኮቻችን ነጻነት በስጦታ የተገኘ ሳይሆን በጀግንነት፣ በአንድነት እና በመስዋዕትነት የተረጋገጠ መሆኑን ያስገነዝቡናል ብለዋል።
ታሪካችን የተሳሰረ እንደመሆኑ ሁሉ የወደፊት እጣ ፈንታችንም እንዲሁ የተሳሰረ ሊሆን ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።
በመደመር መንፈስ፤ኢትዮጵያ እና ኬንያ ለህዝቦቻችን ሰፊ እድሎችን እና የጋራ ብልጽግናን ለመፍጠር በንጹህ ሀይል፣ በመንገድ ትስስር፣ በቴሌኮሙኒኬሽን እና በንግድ ዘርፎች ያለንን ነባር ትብብር ይበልጥ ማጠናከር ይኖርብናል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።
ዛሬ ክብር ለተቸራቸው ጀግኖች ሁሉ፣ ላቅ ያለ አክብሮቴን አቀርባለሁ። መልካም የማሹጃ (የጀግኖች) ቀን ሲሉም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡