በኦሮሚያ ክልል በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመምህራን የስራ ላይ አቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ተጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመምህራን የስራ ላይ አቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ተጀምሯል
አዳማ፤ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራትን በዘላቂነት ለማስጠበቅ ያለመ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመምህራን የሥራ ላይ አቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት መጀመሩን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።
በበይነ-መረብ የሚሰጠው የመምህራን አቅም ግንባታ ሥልጠና ዛሬ በይፋ መጀመሩን አስመልክቶ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ እና የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫው ወቅት የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቡልቶሳ ሂርኮ(ዶ/ር) እንዳስታወቁት፤ የክልሉ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በክልሉ የትምህርት ጥራትን በሚፈለገው ልክ ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በተለይም በእውቀትና በክህሎት የበቃ የሰው ሃይል ለመገንባት በየደረጃው የሚገኙ መምህራን፣ የትምህርት ባለሙያዎችና አመራር አካላት ብቁ የሚያደርጋቸው ስልጠና እንዲያገኙ ትኩረት መሰጠቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ይህንን ለማስፈጸም የሚያስችል ሶፍትዌር በማበልጸግ ከኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዛሬው እለትም በዚህ ሶፍትዌር የተደገፈ የመምህራን የስራ ላይ አቅም ግንባታ ስልጠና በይፋ መጀመሩን ገልጸዋል።
በክልሉ በቅድመ መደበኛ፣ በ1ኛ ደረጃና 2ኛ ደረጃ የሚያስተምሩ መምህራን ባሉበት ሆነው በመመዝገብ በበይነ መረብ አማካኝነት ስልጠናውን እንደሚከታተሉ ገልጸው፤ ይዘቱም በሚያስተምሯቸው የትምህርት ይዘትና በማስተማር ስነ ዘዴ ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል።
ይህም መምህራን በንባብ ራሳቸውን በየጊዜው በማብቃትና ከጊዜው ጋር በመራመድ ብቁ ሆነው ዕውቀታቸውን ለተማሪዎቻቸው በማስተላለፍ ተወዳዳሪና የበቃ ትውልድ ለማፍራት እንዲችሉ ታልሞ መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም በየደረጃው የሚገኙ መምህራን በራሳቸው የይለፍ ስም እየገቡ የተጫነውን የትምህርት ዓይነት በማንበብና የመለማመጃ ጥያቄዎችን በመስራት ካጠናቀቁ በኋላ የብቃት ማረጋገጫ ፈተና እንደሚወስዱ ዶክተር ቡልቶሳ አስታውቀዋል።
ፈተናውን ያለፉ መምህራን የስራ ላይ እድገት፣ ዝውውር፣ ነጻ የትምሀርት እድልና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅም እንደሚያገኙ አመላክተዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎችም ስልጠናው እንደሚያካትታቸው ጠቅሰው ይህም ሴክተሩን መምራት የሚችሉበትን አሰራር በተመለከተ የተዘጋጁ ሞጁሎች ላይ ያተኮረ እና በተከታታይ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ገረመው ሁሉቃ(ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው በመምህራን ልማት ላይ እንዲሰራ በኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ስር የነበሩ 13 የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች ወደ ዩኒቨርሲቲው እንዲቃለቀሉ መደረጉን አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት ኮሌጆቹ ከሠርተፊኬት እስከ መጀመሪያ ድግሪ እያስተማሩ መሆናቸውን ገልጸው የአሁኑንም የመምህራን የስራ ላይ አቅም ግንባታ ስልጠና እንዲያሰለጥን መመረጡን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ይህንን የሚያስፈጽም ኢንስቲትዩት በማዋቀር ለተግባራዊነቱ እየሰራ እንደሚገኝም አክለዋል።
በዚህ ረገድ ለስልጠናው የሚያስፈልጉ የተለያዩ ሞጁሎች እና መጽሐፍት በማዘጋጀትና ሶፍትዌር ላይ በመጫን በየደረጃው የሚገኙ መምህራንን ለማብቃት ዛሬ ስራ ውስጥ መገባቱን አስረድተዋል።
ይህ ልምድ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር የመጀመሪያው መሆኑንም አንስተዋል።
መምህራን የተሰጣቸውን ኮርስ እንዳጠናቀቁ በዩኒቨርሲቲው የተዘጋጀ የብቃት ማረጋገጫ ፈተና እንደሚፈተኑ አስታውቀዋል።