ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸው ግንኙነት እያደገ ነው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

‎‎"አዲስ አጋርነትን ማጠናከር እና የወደፊቱን አብሮ መምራት" በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች (UAE) የ2026 የንግድ እና የኢንቨስትመንት ፎረም እየተካሄደ ነው።


 

‎‎በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ የእስያ እና ፓሲፊክ ሀገራት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ደዋኖ ከድር እንደገለጹት፤በኢትዮጵያ እና በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች መካከል ያለው ግንኙነት እየተጠናከረ ነው።

‎‎የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በአሁኑ ወቅት በአዎንታዊና እጅግ አርአያነት ባለው ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል።

‎ሀገራቱ ያላቸው ግንኙነት ጠንካራና ስትራቴጂያዊ ነው ያሉት ዳይሬክተር ጄኔራሉ፤የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስራቸውም እያደገ መጥቷል ብለዋል።

‎‎ሁለቱ ሀገራት በኢንቨስትመንት ይበልጥ ሊሰሩባቸው የሚችሉባቸው መስኮች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በንግድና ኢንቨስትመንት ያለው ትብብር ወደ አምራች ዘርፍ ሊሰፋ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ባለሀብቶችም በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።


 

በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የሻርጃ ከተማ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ሊቀመንበር አብዱላህ ሱልጣን አል ዖወይስ በበኩላቸው፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።

‎በቀጣይም በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች እና በኢትዮጵያ መካከል በተለያዩ የንግድ ዘርፎችና ምርቶች ላይ የሚካሄደው የንግድ ልውውጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።


 

‎‎በፎረሙ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የሻርጃ ከተማ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

‎‎በፎረሙ ላይ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ባለሀብቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም