ቀጥታ፡

በክልሉ የከተማ መሬት ይዞታ ማረጋገጫና ምዝገባ ስርዓት መዘመኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ ነው

ኮምቦልቻ፤ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የከተማ መሬት ይዞታ ማረጋገጫና ምዝገባ ስርዓትን የማዘመኑ ተግባር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

የአማራ ክልል መሬት ቢሮ የከተማ መሬት ይዞታ የማረጋገጥ፣ የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ሥርዓት ማሻሻል ላይ በኮምቦልቻ ከተማ የንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው።


 

የክላስተር አስተባባሪው ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ በክልሉ ዘመናዊ የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ሥርዓትን በመገንባት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው።

በከተማ መሬት ይዞታ ማረጋገጫና ምዝገባ ሥርዓትን በመተግበር ዘላቂ የመሬት ተጠቃሚነትንና ዋስትናን በማረጋገጥ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት፣ የከተማ ገቢን በማሳደግና አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም በክልሉ ለኢንቨስትመንትና ሌሎች ልማቶች የሚውል መሬትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመዋል።


 

የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ በበኩላቸው፣ በክልሉ ዘመናዊ የከተማ መሬት ይዞታ ማረጋገጫና ምዝገባን በመተግበር የባለይዞታዎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት መቻሉን ጠቁመዋል።

የተገኘውን አበረታች ውጤት አጠናክሮ ወደ 66 ከተሞች ለማስፋት እየተሠራ ነው ብለዋል።


 

በዘጠኝ ከተማ አስተዳደሮች ዘመናዊ የመሬት መረጃ አያያዝ ሥርዓትን በመገንባት ዘርፉን ለማዘመን ወደ ሥራ መገባቱን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን መሬት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዱራህማን ይመር ናቸው።

ከተሞችን በማዘመን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ወርቃለማሁ ኮስትሬ በበኩላቸው፤ በከተማዋ የተጀመረው ዘመናዊ የከተማ መሬት ይዞታ ማረጋገጫና ምዝገባ ሥርዓት ውጤት አስገኝቷል ብለዋል።

በዚህም የመልካም አስተዳደር ችግርን ከማቃለል ባለፈ ሕገወጥ የመሬት ወረራን፣ ሕገወጥ ግንባታንና ብልሹ አሠራርን በማስቀረት ረገድ ውጤታማ ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የክልል፣ የዞንና የከተማ አመራሮችንና ባለሙያዎችን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም