ቀጥታ፡

ሁለንተናዊ ልማትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

መቱ ፤ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ)፦ የሀገር ግንባታንና ልማትን በማረጋገጥ የዜጎችን ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረሻድ ከማል (ዶ/ር) ተናገሩ።

በኦሮሚያ ክልል በተከናወነው አዲስ የዞኖች አወቃቀር መሠረት ለደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን የተመደቡ አመራሮች በመቱ ከተማና በአጎራባች ወረዳዎች ከነዋሪዎች ጋር ትውውቅ አድርገዋል።


 

ዋና አስተዳዳሪው በወቅቱ በኦሮሚያ ክልል የተካሄደው አዲስ የዞኖች መዋቅር ዋነኛ ዓላማ የሕብረተሰቡን ሕይወት መቀየርና ከድሕነት ለማላቀቅ የሚያስችሉ አሰራሮችን ለመዘርጋት መደላድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

የሀገር ግንባታ እና ልማትን በማረጋገጥ የዜጎችን ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ በተለይም ከተለመዱ የስራና የአሰራር ልማድና ባሕሎች መላቀቅ የግድ መሆኑን ዶክተር ረሻድ አጽንዖት ሰጥተዋል።

ሁለንተናዊ ልማትና ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው በመንግስት ብቻ ሳይሆን የሁሉንም የነቃ ተሳትፎና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ በመሆኑ የሕብረተሰቡ የልማትና የሰላም ተሳትፎ ተጠናክር እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በዚህም የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ተሰሚነቷን ይበልጥ ለማሳደግ በሁሉም መስኮች የሚሰራው ስራ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዲዳ ጉደታ በበኩላቸው፤  የህብረተሰቡ ጥያቄ የመሠረተ ልማት፣ የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ልማት ተደራሽነና ተጠቃሚነት በመሆኑ ለዚህ ትልቅ ኃላፊነት ይጠብቀናል ብለዋል።

በአዲሱ አደረጃጀት የስራ ኃላፊነት የተሰጣቸው አመራሮችም የሕብረተሰቡንና የሀገርን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ አክለዋል።

የሕብረተሰቡን የኢኮኖሚ አቅም በማደራጀት ኑሮውን በማሻሻልና የኑሮ ውድነት ችግሮችን ለመቅረፍ  አዲሱ የዞኖች መዋቅር የበለጠ ወደ ሕብረተሰቡ ለመቅረብ የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

የመቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ተሻለ ኤጄርሶ፤ በክልል ደረጃ የተከናወነው የዞኖች አደረጃጀት ሁለንተናዊ ልማትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በአዲሱ መዋቅር የታሰበው ግብ እንዲሳካ የከተማ አስተዳደሩ በበለጠ ትኩረት ይሰራል ሲሉ ገልጸዋል።

አዲሱ የዞኖች አወቃቀር የዜጎችን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይበልጥ ወደሕብረተሰቡ በቀረበ መልኩ ይሰራል የሚል እምነት እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ የመርሃግብሩ ተሳታፊ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም