ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ የዲፕሎማሲ አቅም ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ሰጭነትና ተደማጭነት እንድትሸጋገር እያስቻላት ነው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ የዲፕሎማሲ አቅም ቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በማጎልበት ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ሰጭነትና ተደማጭነት እንድትሸጋገር እያስቻላት መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

ምሁራኑ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬትም የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን ምላሽ ማስገኘት የሚያስችል ዓለም አቀፍ ቅቡልነት ማሸጋገር እንዳስቻለ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ሔኖክ ስዩም (ዶ/ር)፤ ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር የአንድ ሀገር ማዕከላዊ የሉዓላዊነት ምሰሶ ነው ብለዋል።

የወቅቱ የኢትዮጵያ መሠረታዊ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ የባሕር በር ባለቤትነትን በማስመለስ በተሳለጠ የወጪና ገቢ ንግድ ሥርዓት የኢኮኖሚ ዕድገትን ማፋጠን መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኃይልና የመሠረተ ልማት ትስስር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄዋን ቅቡልነት እንደሚሳይ ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የተጀመረው የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የልማት ተነሳሽነት (HoAI) በቀጣናው ላለው የዲፕሎማሲ ግንኙነትና ትስስር ትልቅ ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ከአጀንዳ ተቀባይነት አጀንዳን በመቅረጽ የቀጣናውን ሀገራት የንግድ፣ የመሠረተ ልማትና የተቋማት ግንባታ ውጤታማነትን ለማላቅ የሚያግዝ አቅም እየፈጠረች መሆኗን እንደሚያሳይ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር የጎረቤትና ወዳጅ ሀገራት እንዲሁም የተቋማት መልካም ግንኙነት የዲፕሎማሲ ትብብር የተጻራሪ ኃይሎችን አቅም እየኮሰመነ መሆኑን አስረድተዋል።

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በተጻራሪ በመቆም የሀገርን መሻት ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካላትም በተመዘገበው የዲፕሎማሲ የበላይነት ቦታ እያጡ መምጣታቸውን አብራርተዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት በማረጋገጥ ሁለንተናዊ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር የተመዘገቡ ስኬቶችን ማላቅ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።


 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝምና አስተዳደር መምህርና ተመራማሪ ተስፋዬ ጂማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የመደመር መንግሥት ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር አቅም እያጎለበተ ነው ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግንባታ ስኬትም በመንግሥት የዲፕሎማሲ ጥረት የተሳካና የሀገርን በሰላምና ትብብር ላይ የተመሠረተ የዲፕሎማሲ አካሄድ በተግባር የገለጠ መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር የሕልውና ጉዳይ ነው ያሉት ምሁሩ፤ የነበራትን የባሕር በር ለማስመለስ የቀረበው ጥያቄም ታሪካዊና ሕጋዊ አምክንዮ ያለው ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን ቀጣናዊ በጎ ተጽዕኖ በመረዳት የባሕር በር ባለቤትነት አስፈላጊነትን ዓለም ተገንዝቧል ያሉት ደግሞ የሥነ-አመራርና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ጌትዬ ትርፌ (ዶ/ር) ናቸው።


 

መንግሥት ባለፉት ዓመታት ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ ሕጋዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ መልክዓ ምድራዊና ምክንያታዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም በአጭር ጊዜ ዓለም አቀፍ ቅቡልነት ማግኘቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ዓለም አቀፍ ቅቡልነትም በመንግሥት የዲፕሎማሲ ጥረት የተገኘ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር አቅም የፈጠረ፣ የውሃ ፖለቲካና ዲፕሎማሲያዊ የመደራደር አቅምን ያጎለበተ የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክት መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነትም የዲፕሎማሲ አቅምን በማጎልበት የመንግሥትና ሕብረተሰብ ትብብር ለዲፕሎማሲ፣ ፖለቲካና ኢኮኖሚ መጠናከር ወሳኝ መሆኑን ያመላከተ ነው ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም