ቀጥታ፡

የሆለሌ ጨዋታ

በኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ተጠብቀው የቆዩ በርካታ ባህላዊ እሴቶች አሉ፤ እነዚህ ቱባ ባህሎች የሕዝቦችን ማንነት፣ የኑሮ ዘይቤ፣ የፍቅር አገላለጽ፣ የማኅበራዊ ግንኙነትና የጋራ ኑሮ የሚያንጸባርቁ የታሪክ ማኅደሮች ናቸው። በደቡብ ወሎና አካባቢው የሚታወቀው የሆለሌ ጨዋታም ከእነዚሁ መካከል ይጠቀሳል።

የሆለሌ ጨዋታ የወጣቶች መገናኛ፣ የፍቅር መግለጫ እንዲሁም የባህላዊ አለባበስና ውበት መግለጫ መድረክ ነው። በዚህ ባህላዊ ጨዋታ የአካባቢው ሕዝብ ማንነት፣ የማኅበረሰቡ የጋራ ሕይወትና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉ እሴቶች በግልጽ ይንጸባረቃሉ።

የሆለሌ ጨዋታ ምንድን ነው? ከሚለው ስንነሳ፤ በደቡብ ወሎና አካባቢው በየዓመቱ በጥር ወር የሚከበር የወጣቶች ባህላዊ ጨዋታና የአደባባይ በዓል ነው። ከበዓሉ ዋነኛ መለያዎች መካከል የወጣቶች ዜማ፣ ባህላዊ አለባበስና ውበት፣ የሎሚ ውርወራና የወንዶች ትግል ይጠቀሳሉ። የሆለሌ የመጨዋቻ ስፍራ በተንጣለለ ሰፊ ሜዳ ላይ የሚካሄድ ነው። በሜዳው ላይ ለሴቶች የዜማና የውዝዋዜ ቦታ፣ ለወንዶች ደግሞ በትግል የሚፈታተኑበት የተለየ ስፍራ ይኖራል። 

በሆለሌ ባህላዊ ጨዋታ ወጣት ሴቶች ፀጉራቸውን ሹርባ ተሰርተው፣ አምረውና ተውበው ይቀርባሉ። ውበታቸውን የሚያጎሉ ጌጦችንና አለባበሶችን ይጠቀማሉ። ከአደስ ቅጠል ተወቅጦ በተዘጋጀ በተለምዶ “ቁኒ” በሚባለው የተለወሰ ቅቤ ፀጉራቸውን ይቀባሉ። በዚህ መልኩ ወደ ጨዋታው ሜዳ በመሄድ “እሆለሌ….” እያሉ የተለያዩ ግጥሞችን በመደርደር ያዜማሉ። 


 

የሚያሞካሹትን ወንድ….

እሆለሌ አንተ ጎብላላ፣ አንተ ሸበላ

ለምን አትመጣም ምሳ እንድንበላ። በማለት ሲያወድሱት፤ የሚነቅፉትን ወንድ ደግሞ….

ይሄ ምን ይላል ጎፈሬው ዋሾ

ሲሸሽ አየሁት ጌሾ ለጌሾ። በማለት ፍርሃቱን ይገልጹታል። 

የሆለሌ ጨዋታ ሲከናወን ወጣት ሴቶች እጅ ለእጅ ተያይዘው ክብ ሰርተው እየዞሩ “እሆለሌ!” በማለት ያዜማሉ። በዜማው ውስጥ የደስታ፣ የአንድነት መንፈስና የባህል ውበት ይታያል። የዜማው ምት፣ የወጣቶቹ እንቅስቃሴና በዙሪያቸው ተኮልኩለው በቂቤ የተወለወለ ዱላ ይዘው አሻግረው የሚለከቱ ወጣት ወንዶች የባህላዊ ጨዋታው ሌላ ውበት ናቸው።

ከምሳ በኋላ በተንጣለለው ሜዳ ላይ የሚካሄደው የሆለሌ ጨዋታ ከሚታወቅባቸው ልዩ ገጽታዎች መካከል ሎሚ የመወርወር ልማድ አንዱ ነው። በበዓሉ ላይ ከተገኙ ወጣት ወንዶች መካከል ለእጮኛ የደረሰና የትዳር ፍላጎት ያለው ከሆነ ቀልቡ ያረፈባትና የወደዳት ልጃገረድ ላይ ሎሚ ይወረውራል። ይህ ልማድ የፍቅርን ፍላጎት በባህላዊ መንገድ የማሳወቅ ልዩ ዘዴ ነው። 

አንዳንድ ጊዜ አንዲት ወጣት በሁለት ወንዶች የምትወደድ ከሆነ ሁለቱም ሎሚ ሊወረውሩባት ይችላሉ። የወጣቷ ወዳጅ ወይም የወደፊት የትዳር አጋር የሚሆነው ግን በትግል ተፈታትነው አሸናፊ የሆነው ወጣት ይሆናል።

በሆለሌ በዓል የወንዶች ትግል የራሱ የሆነ ስፍራ አለው። ወጣት ወንዶች ወፈር ብሎ አምሮ ተውቦ የተዘጋጀ ዱላ ይዘው፣ ጎፈሬያቸውን አስተካክለው፣ ሚዶ ሰክተው ወደ መጫወቻው ስፍራ ይመጣሉ። በዚያም በአካል ብቃትና በትግል ክህሎታቸው ይፈታተናሉ። ይህ ትግል ከአካላዊ ውድድር ባሻገር የወጣቶችን ድፍረት፣ ብቃትና በባህላዊ ጨዋታ የመሳተፍ ፍላጎት የሚያሳይ ነው። በተመሳሳይ ወቅት ተጋጣሚዎች እርስ በርስ እንዲከባበሩ፣ ለውድድር ሕጎች እንዲገዙና አሸናፊውንም ሆነ ተሸናፊውን በክብር እንዲቀበሉ የሚያግዝ መልካም እሴት የሚገነባበት ነው።


 

የወሎ ሕዝብ በሥነ ጽሑፍ፣ በሙዚቃ፣ በባህላዊ አለባበስ፣ በግጥምና በተለያዩ ማኅበራዊ ልማዶች የበለጸገ ባህላዊ ሀብት አለው። ሆለሌም ከእነዚህ የማንነት መገለጫዎች መካከል ተጠቃሽ ነው። ባህሉ በወጣቶች መካከል የመተዋወቅ ዕድል ይፈጥራል፤ የማኅበረሰቡን የጋራ ስሜት ያጠናክራል፤ በተጨማሪም በባህላዊ ሙዚቃና ውዝዋዜ የተሰጡ ተሰጥኦዎች እንዲገለጹ መድረክ ይሆናል። በዓሉ ለወጣቶች የደስታ ጊዜ ሲሆን ለአዛውንቶች ደግሞ ያለፈውን ዘመንና የባህል ትውስታ የሚያድስ አጋጣሚ ነው።

የባህል ጨዋታ ዘላቂነት ከተግባሩ ብቻ ሳይሆን ከዜማው፣ ከግጥሙና ከትውልድ ትውልድ ከሚተላለፉ ትውስታዎችም ጋር ይያያዛል። የወሎ ላሊበላ ኪነት አባል የነበረችው ዙሪያሽ አብዩ “እሆለሌ” እያለች የዘፈነችለት ዜማ የዚህ ባህል የጥበብ ገጽታ መታወሻ ነው። የሆለሌ ዜማ በድምፅ ብቻ የሚሰማ የዘፈን ሥራ ሳይሆን የባህል ታሪክን፣ የሕዝብ ስሜትንና የማኅበረሰቡን እሴት የሚያንፀባርቅ ትውፊታዊ ጥበብ ነው።

ባህል የማንነት ምንጭ ብቻ አይደለም፤ በትክክል ከተጠበቀና ከተደራጀ የኢኮኖሚ እድልም ይፈጥራል። በደቡብ ወሎ የሚካሄደው የሆለሌ ጨዋታም በቱሪዝም ዘርፍ ያለው አቅም በተገቢው መንገድ ከተጠቀምንበት አካባቢው ለሌሎች በስፋት እንዲታወቅ የሚያግዝ ይሆናል። በዓሉን በተደራጀ መልኩ ለማስተዋወቅ ከተሠራ በየዓመቱ የባህል ቱሪስቶችን፣ ተመራማሪዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ የሥነ ጥበብ ባለሙያዎችንና የባህል አፍቃሪዎችን ወደ አካባቢው ለመሳብም ያስችላል።

ከተለያዩ ማኅበራዊ ለውጦች ጋር በተያያዘ በብዙ አካባቢዎች የቆዩ ባህላዊ ጨዋታዎችና ልማዶች የቀድሞ ተወዳጅነታቸውን እያጡ ይገኛሉ። የሆለሌ ጨዋታም ከዚህ ፈተና ነፃ አይደለም ማለት ይቻላል።

የከተማ ኑሮ መስፋፋት፣ የወጣቶች የመዝናኛ ምርጫ መለወጥ፣ የዘመናዊ ሚዲያዎች ተጽዕኖ፣ የባህላዊ ዕውቀት ማስተላለፊያ መንገዶች መዳከምና ሌሎችም ምክንያቶች ለባህላዊ ጨዋታዎች መቀዛቀዝ ምክንያት ሆነው ይጠቀሳሉ። የሆለሌ ጨዋታም በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥ ያለ፤ ነገር ግን መረሳት የሌለበት አስደናቂ ባህላዊ ጨዋታ መሆኑን መናገር ይቻላል።

በመሆኑም የሆለሌ ጨዋታ ዳግም እንዲያንሰራራ በተለይም የባህልና ቱሪዝም ባለሙያዎች፣ የአካባቢው አስተዳደሮች፣ የአካባቢ ሽማግሌዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ትምህርት ቤቶችና የወጣቶች ማህበራት በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። በአቅራቢያ የሚገኘው የወሎ ዩኒቨርሲቲ የሆለሌ ጨዋታን በመመዝገብ ማጥናት፣ የዜማ አወራረዱን፣ ግጥሙን፣ የአለባበስ ልማዶችና የበዓሉን ማኅበራዊ እሴት ማጥናት ተገቢ ይሆናል።

የሆለሌ ክበባትን በትምህርት ቤቶችና በወጣት ማኅበራት በማቋቋም የባህል እውቀት ማስተላለፊያ ሥራዎችን ማካሄድ ይቻላል። የጥር ወር የሆለሌ አከባበር ዓመታዊ መርሐ ግብር ጋር በማያያዝ የተለየ የጨዋታ ስፍራ በማዘጋጀት ማክበር ይቻላል። በሚዲያ እና በተለያዩ የዲጅታል አማራጮች ሆለሌን የማስተዋወቅ ስራ በስፋት መስራት ያስፈልጋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም