በወላይታ ዞን ለሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በወላይታ ዞን ለሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል
ወላይታ ሶዶ፤ ጥቅምት10/2019 (ኢዜአ)፡-በወላይታ ዞን ለሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም መፈጠሩን የዞኑ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አዲሱ ሶርሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ ለሚያጋጥሙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በማንኛውም ጊዜ ሊፈጠሩ የሚችሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል በተከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችም አበረታች ውጤት መገኘቱም ተናግረዋል።
በተለይ ችግር ሲገጥም ጥቅም ላይ የሚውል የሰብል ምርት ለማምረት በተከናወኑ የግብርና ልማት ሥራዎች ከ30 ሺህ ኩንታል በላይ የመጠባበቂያ እህል ክምችት ለመያዝ ተችሏል።
በዞን ደረጃ ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ የመያዝ አቅም ባላቸው ሁለት መጋዘኖች እህሉ የማከማቸት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ኃላፊው አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡
እስከ ሕዳር ወር 2019 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ 373 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካሁን በተደረገ ጥረት 160 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መቻሉንም አቶ አዲሱ አመልክተዋል።
በዚህም ለተገኘው ውጤት በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አመራሮች፣ ሠራተኞች፣ የተለያዩ ማህበራትና ህብረተሰቡ ጭምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
"ለችግር ወቅት የሚሆኑ ምግብ ነክ ያልሆኑ ግብዓቶችን የማሰባሰብ ሥራም እየተከናወነ ይገኛል" ያሉት የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ፣ እስካሁንም ከ3 ሺህ 900 በላይ የተሟላ የቤት ቁሳቁስ ለማሰባሰብ ተችሏል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም በ2 ሺህ 100 ሄክታር ማሳ ላይ በቆሎ፣ ማሾ፣ ጤፍና ካሳቫ በማልማት የእንክብካቤ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዞኑ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት መረጃ እንደሚያሳየው በዞኑ ባሉ መዋቅሮች በተደራጀ መልኩ እህል የማሰባሰብና ሀብት የማከማቸት ተግባር በልዩ ትኩረት እየተከናወነ ይገኛል።