በክልሉ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ ምርቶች የማምረት ሥራው ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ ምርቶች የማምረት ሥራው ይጠናከራል
ዱራሜ፤ ጥቅምት 10/2019(ኢዜአ):-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉአላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ ምርቶችን የማምረት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ገለፁ።
"የተቀናጀ ግብርና፤ ትጋት ለተመጣጠነ ምርታማነት" በሚል መሪ ሀሳብ በበጋ ወቅት የተቀናጀ የግብርና ልማት ሥራዎች የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ በዱራሜ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ያሉ ፀጋዎች በአግባቡ አልምቶ በመጠቀም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል።
ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን የማሳደግና እሴትን ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ሥራ እየተጠናከረ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡
በተለይም በክልሉ በበጋ ወቅት ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ በተጨማሪ ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆኑ ምርቶችን የማምረት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በበጋ ወቅት የሚከናወኑ የግብርና ልማት ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ አመራሩ በቅንጅት መምራት እንዳለበትም ርዕስ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው፣ መንግስት በግብርናው ዘርፍ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ባሉ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤት መመዝገባቸውን አንስተዋል።
በዚህም ክልሉ ያሉትን ፀጋዎች አልምቶ እንዲጠቀምና የግብርና ልማት ሥራን ከዝናብ ጥገኝነት በማውጣት በዓመት ከ3 ጊዜ በላይ ለማምረት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
በተለይ የበጋ ወቅት ግብርና ልማት ሥራዎች ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የአርሶ አደሩን ገቢን በማሳደግ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
የመድረኩ መዘጋጀት በዘርፉ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የጋራ መግባባት ላይ እዲደረስ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ነኢማ ሙኒር ጨምሮ የክልሉ፣ የዞንና የወረዳ የሥራ ሀላፊዎች እና ሞዴል አርሶ አደሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።