ቀጥታ፡

የቁሉምሳ ግብርና ምርምር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጥረት እየደገፈ ነው

አሰላ፤ጥቅምት 10/2019(ኢዜአ )፦በምርምር የሚያፈልቃቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የስንዴ ምርታማነትን ለማሳደግና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እየደገፉ መሆናቸውን የቁሉምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ገለጸ።

በብሔራዊ የስንዴ ልማት የመስክ ቀን በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ጢዮ ወረዳና ቁሉምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ጉብኝት እየተካሄደ ይገኛል።

የቁሉምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ አለማየሁ በወቅቱ እንደገለፁት፤ ማዕከሉ ከ80 በመቶ በላይ የስንዴ የመነሻ ዘር ብዜትን በራሱና በአርሶአደሩ ማሳ ላይ እየተገበረ ይገኛል።

ማዕከሉ ከዘር ብዜት ባለፈ ቢጫ ዋግን ጨምሮ የሰብል ምርትና ምርታማነትን መቀነስ የሚችሉ በሽታዎችን የሚቋቋሙ የስንዴ ዘረመሎች ብዜት ላይ እየሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።

በተጨማሪም ድርቅና ሙቀትን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡ የስንዴ ዝርያ በማባዛት ለአርሶአደሩና አርብቶ አደሩ በስፋት ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ለዚህም የበጋ መስኖ ስንዴና የቆላማ አከባቢ የስንዴ ዝርያዎች ከማዕከሉ በምርምር እየወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም "በሀገራችን የስንዴ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተወጣን እንገኛለን" ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ከአምስት ሺህ ኩንታል በላይ የስንዴ መነሻ ዘር አባዝተን በየዓመቱ ለአምራች ድርጅቶችና ተጠቃሚዎች እያቀረብን ነው ብለዋል።


በተለይም የስንዴ ኤክስፖርት አቅምን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ሽመልስ፤ ለዚህም ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወንን እንገኛለን ብለዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰብል ልማት ዳይሬከተርና ተወካይ ፍቃዱ ጉርሙ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ኢንስቲትዩቱ በስንዴ ልማት ላይ አዳዲስ አሰራርና ቴክኖሎጂዎችን ስራ ላይ እንዲውሉ ለባለድርሻ አካላት ተደራሽ በማድረግ በምርታማነቱ ላይ ተጨባጭ ውጤት እንዲመጣ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።

በተለይም ለበጋ መስኖና በሀገሪቷ ቆላማ አካባቢዎች ስንዴ በመስኖ በስፋት እንዲመረት በማድረግ በስንዴ ምርት እራሳችንን እንድንችል የጎላ ሚና እየተወጣን እንገኛለን ብለዋል።

ቴክኖሎጂን በማፍለቅና በማስፋፋት በተለይም የስንዴ የመነሻ ዝሪያዎችን በማባዛትና ተደራሽ በማድረግ በምርትና ምርታማነት ዕድገት ላይ ተጨባጭ ውጤት እንዲመጣ እየተወጣን ያለነውን ሚና አጠናክረን ለማስቀጠል ያለመ ብሔራዊ የመስክ ቀን መሆኑንም ተናግረዋል።

በጉብኝቱ ላይ የዘርፉ አመራሮችና ተመራማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ አርሶአደሮችና አጋር አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም