የባሕር በር ባለቤትነት ለሁለንተናዊ ተጠቃሚነታችን ወሳኝ ነው-የሰመራ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የባሕር በር ባለቤትነት ለሁለንተናዊ ተጠቃሚነታችን ወሳኝ ነው-የሰመራ ከተማ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፣ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት የንግድ እንቅስቃሴን ጨምሮ ለሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸው ዋስትና መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰመራ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ፣በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች የምትገኝ እና የቀጣናው የጂኦ-ፖለቲካዊ መረጋጋት ዋና መሠረት ነች።
የኢትዮጵያ፣የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ ሀገራዊ ሕልውናንና ደህንነትን የማረጋገጥ፣ የልማትና ብልፅግናን ጉዞ ዕውን የማድረግ የትውልድ ጥያቄ ነው።
ትልቅ አቅም ያላት ኢትዮጵያ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት የነበራት የባህር በር ባለቤትነት እና የማሪታይም መብት በሕጋዊና በዲፕሎማሲያ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ እየሰራች ነው።
ይህ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ወሳኝ ምዕራፍን የሚከፍት ነው።
የአፋር ሰመራ ከተማ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የህልውና ጉዳይ ነው።
ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ አንዋር አሊ የባሕር በር ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሰመራ ከአሰብ ወደብ ጋር ያላት የጂኦግራፊ ቅርበትንም በአብነት ገልጸዋል።
ይህም ለክልሉ ተጨማሪ ዕድል እንደሚፈጠር ተናግረዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ አደም መሐመድ ሁሴን በበኩላቸው፣ የባሕር በር ባለቤትነት ለኢትዮጵያ የንግድና የኢኮኖሚ ጥቅም እንደሚያስገኝ ገልጸዋል።
የወደብ አገልግሎት ወጪን በመቀነስ ለሌሎች ሀገራዊ የልማት ፍላጎቶች የሚውል ሀብት ሊያሳድግ እንደሚችልም አስረድተዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ሁሴን አህመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የባሕር በር ባለቤት መሆን ለሀገሪቱ የጂኦፖለቲካዊ ጥቅም ከማስገኘቱ ባሻገር ለአፋር ክልል የንግድ፣ የትራንስፖርት፣ የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን ለማሳደግ ትልቅ እድል እንዳለው ገልጸዋል።
የባሕር በር መዳረሻ መኖሩ የንግድ መስመሮችን በማስፋፋት ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የገለጹት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ዘይናብ አሊ ኢብራሂም ናቸው።
በከተማዋ ያለው የጭነት የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ከወደብ ጋር በሚኖር የተሻለ ትስስር የበለጠ ሊያድግ እንደሚችልም አመልክተዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ሙህዲን አሚን እንዳሉት፣ የባሕር በር መዳረሻ ማግኘት ከኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ በተጨማሪ ህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
ነዋሪዎቹ የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጥቅምና ለአፋር ክልል የልማት ዕድሎች ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ፣ጥያቄው በሰላማዊና በዘላቂ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኝ ያላቸውን ፍላጎት አንጸባርቀዋል።