የሕዝብ ስቃይ ይቁም ብለን ሰላምን መርጠናል-የሰላም አማራጭን የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ስቃይ ይቁም ብለን ሰላምን መርጠናል-የሰላም አማራጭን የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች
አዲስ አበባ፣ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ይንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ የታጠቁ ኃይሎች በአሁኑ ወቅት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ማኅበረሰቡ በመቀላቀል ላይ ይገኛሉ።
በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ የሰላምን አማራጭ ተቀብለው ከተመለሱት ወጣቶች መካከል ተቀባ አየለ አንዱ ነው።ራሱን ጨምሮ 75 ወጣቶች በተሳሳተ መንገድ ወደ ጫካ መግባታቸውን ያስታውሳል።
ቀደም ሲል በጫካ በነበሩበት ወቅት ሕዝቡን ላልተገባ ስቃይ፣ እንግልት እና በደል ሲዳርጉ መቆየታቸውን አልሸሸገም።ይሁን እንጂ ካለፈው ስህተት ተምረው የሕዝባቸውን ዕንባ ለማበስ እና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ቃል እንደገቡ ተናግሯል።
ሌላኛው የቀድሞ ታጣቂ ጋሻው ወልዴ በበኩሉ በግለሰቦች ግፊት እና ጫና ምክንያት የትግሉ ዓላማ ሳይገባን ለሦስት ዓመት ያህል በጫካ ቆይተናል በማለት የነበረውን ሁነት በጸጸት ገልጿል።
ይህ የተሳሳተ መንገድም የወጣትነት ጊዜያቸውን እንደበላው እና በልማት ተሰማርተው ሃብት ማፍራት እና የሕዝባቸውን ሰላም መጠበቅ ሲገባቸው የገዛ ወገናቸውን በሰላም እጦት መበደላቸውን በጸጸት ተናግሯል።
የጫካው ትግል የሕዝብን ስቃይ ማራዘሚያ፤ የግለሰቦች ጥቅም ማስጠበቂ እና የእርስ በርስ መጠፋፊያ መኾኑን በመረዳት ወደ ሰላም እና ልማት ተመልሰናል ነው ያለው።
በመተማ ወረዳ በበጀት ዓመቱ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ባደረጉት የማያቋርጥ ጥረት በርካታ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ማኅበረሰቡ የተቀላቀሉ መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የወረዳው ሰላም እና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስማማው አባተ ናቸው።
በቀጣይም የቀሩ ወጣቶች ወደ ሰላማዊው ሕይወት እንዲመለሱ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን እና የተመለሱትን ወጣቶች በንግድ፣ በእርሻ እና በልማት ሥራዎች ላይ የማደራጀት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።