ቀጥታ፡

የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት በአዳዲስ ዘርፎች ማሳደግ የሚያስችላቸው ምቹ ምህዳር ተፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ)፦የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት በአዳዲስ ዘርፎች ማሳደግ የሚያስችላቸው ምቹ ምህዳር መፈጠሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው ሀሰን መሀመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

"አዲስ አጋርነትን ማጠናከር እና የወደፊቱን አብሮ መምራት" በሚል መሪ ሀሳብ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች እና የኢትዮጵያ የንግድ ልዑካን የ2026 የንግድ ፎረም በመካሄድ ላይ ይገኛል።

‎በፎረሙ የመክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሀመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የንግድ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ በመገኘት  የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚያዊና ንግድ ግንኙነት ለማጠናከር ያሳየው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው።

ፎረሙ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር፣ የኢኮኖሚ ትብብርን ለማስፋፋት እና አዳዲስ አጋርነቶችን ለመፍጠር ትልቅ ዕድል እንደሚከፍት ገልጸዋል።

የኤሚሬቶች ኩባንያዎች ያሏቸውን የቴክኖሎጂ፣ የፋይናንስ እና የሎጂስቲክስ አቅሞች በመጠቀም በኢትዮጵያ በቱሪዝም፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በኮንስትራክሽን ዘርፎች የሚያደርጉት ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽንን ለማፋጠን፣ ማኑፋክቸሪንግን ለማስፋፋትና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የምታደርገው ጥረት የዓለም አቀፍ ንግድና ኢንቨስትመንት ማዕከል የመሆን ራዕይዋን የሚያጠናክር እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ተመራጭ የሚያደርጓትን የተፈጥሮ ሀብት፣ አመቺ አየር ጠባይ፣ እንዲሁም ሰፊና ተወዳዳሪ የሰው ኃይልና የኢንቨስትመንት ዕድሎች እንዳሏትም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ለግብርና፣ ለታዳሽ ኃይልና ለኢንዱስትሪ ልማት የሚሆኑ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብቶችና ተስማሚ አየር ጠባይ ያላት መሆኑ፣ የመሰረተ ልማትና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

‎የመደመር መንግሥት የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ለማስፋት በትራንስፖርት፣ በኃይል አቅርቦት፣ በሎጂስቲክስና በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፎች ላይ ሰፊ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችንና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት በአዳዲስ ዘርፎች ይበልጥ የሚያድግበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።

ይህ የንግድ ፎረም የሁለቱን ሀገራት የጋራ ልማትና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር አዲስ የትብብር ምዕራፍ እንደሚከፍት ተገልጿል።

በፎረሙ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች አልሚዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም