የማዕድ ማጋራትና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊ እሴቶችን ለማጠናከር ከፍተኛ ፋይዳ እያበረከቱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የማዕድ ማጋራትና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊ እሴቶችን ለማጠናከር ከፍተኛ ፋይዳ እያበረከቱ ነው
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ)፦በመንግሥት የተጀመሩ የማዕድ ማጋራት፣ የበጎ ፈቃድና ሌሎች የበጎ አድራጎት ስራዎች ማህበራዊ እሴቶችን እንደገና ለማጠናከርና ለማደስ ከፍተኛ ፋይዳ እያበረከቱ መሆኑን የሀይማኖት አባቶች እና የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ገለጹ።
እነዚህ በጎ ተግባራት ሰብዓዊነትን፣ ሀገራዊ ፍቅርንና የህዝቦችን አብሮነት ይበልጥ ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።
መንግሥት ለእነዚህ ሀገራዊና ማህበራዊ እሴቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ አበረታች ውጤቶችም መመዝገብ ችለዋል።
በተለይም አቅመ ደካሞችንና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በመደገፍ፣ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በመገንባትና ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ ስራዎች በማሰማራት ረገድ ተጨባጭ ለውጦች ታይተዋል።
እነዚህን የተጀመሩ በጎ ስራዎችና ማህበራዊ እሴቶች ዘላቂ ለማድረግ የመንግሥት ጥረት ብቻውን በቂ ባለመሆኑ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪል ማህበራት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሂደቱ ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳላቸው ይገለጻል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች በኢትዮጵያ የነበሩትን የመተጋገዝና የአብሮነት እሴቶች ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ ጠንካራ ማህበራዊ እሴትን ለትውልድ ለማስተላለፍ የሁሉንም ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ክፍል ዋና ኃላፊ መልአከ ገነት ልሳነ ወርቅ ተስፋ፣ በኢትዮጵያ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የቆዩት የመቻቻል፣ የመተጋገዝና የመከባበር እሴቶች ለሀገር አንድነት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
እሴቶቹን ለማጎልበት በመንግሥት በኩል በተከናወኑ የተለያዩ ስራዎች በአሁኑ ወቅት አዎንታዊ ለውጦች እየታዩ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመሆኑም በቤተ እምነታቸው በኩል ለሀገር አንድነት ወሳኝ የሆኑ እሴቶች እንዲጠበቁ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፣ እሴቶቹ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ ሁሉም በትብብር መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የአስተዳደር ጉዳዮችና ተቋማዊ ልህቀት ምክትል ፕሬዚዳንት ኡስታዝ ሼህ አቡዲን ሼህ ኑሬ፣ ማህበራዊ እሴቶች ማህበረሰብን የሚያስተሳስሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ የማዕድ ማጋራትና የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን በማስፋትና በማጎልበት በተሰራው ስራ አብሮነትን የሚያጠናክሩ አዎንታዊ ለውጦች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር መጋቢ አሸብር ከተማ በበኩላቸው፣ በማህበራዊ እሴቶች ግንባታ የሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል።
በመሆኑም በእነዚህ እሴቶች ዙሪያ በቀጣይም በርካታ ስራዎችን መስራት እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አህመድ ሁሴን በበኩላቸው፣ ማህበራዊ እሴቶች የአንድ ሀገር እና ህዝብ መገለጫ መሆናቸውን አንስተዋል።
በመሆኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ የማህበራዊ እሴቶቻችን ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ጥናት ላይ የተመሠረቱ ተግባራዊ ሥራዎች ማከናወን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማህበር ፕሬዝዳንት እናትአለም እንዳለ፣ማህበሩ ከባለ ድርሻ አካላትጋር በመተባበር በዕውቀት እና በስነ-ምግባር የታነፀ ሀገር ወዳድ ትውልድ ለመፍጠር በርካታ ተግባራትን እንደሚያከናውን ጠቅሰዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት ወቅት የመተጋገዝ እና የመደጋገፍ ባህል መጎልበቱንም አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንት በረከት ብርብርሳ ወጣቶች የመረዳዳት፣ የመቻቻል ፣የበጎ ተግባራትንና ሌሎች የማህበራዊ እሴቶች እንዲያጎለብቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሰራቱ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
ሀገራዊ እሴቶቻችን በኢትዮጵያ ወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ዳግም እየታደሱና እየተጠናከሩ መምጣታቸውን ተናግረዋል።