ቀጥታ፡

ውቢቷ ባህር ዳር በጣና ፎረም ዋዜማ

ከብሩህ ኮከብ (ከባህር ዳር ኢዜአ ቅርንጫፍ)

ጣናን ትራሷ፤ አባይን መቀነቷ አድርጋ የተመሰረተችው ውቢቷ የባህር ዳር ከተማ የጎብኚዎችን ቀልብ የመሳብ የተፈጥሮ ኃይል የተቸራት ከተማ ናት።

ከተማዋ በጣና ኃይቅ ውስጥ የሚገኙ ደሴቶችንና ገዳማትን፣ የጭስ አባይ ፏፏቴን በመጎብኘት ለመዝናናት ማዕከል ሆና የሚመጣውን የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚ እያስደሰተች ትሸኛለች።

በቅርቡ ማስፋፊያ የተደረገለት የበላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ አዲሱ የአባይ ድልድይ፣ የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምና በከተማዋ የተገነባው የኮሪደር ልማት ከተፈጥሮ መስህቧ ጋር ተዳምሮ ተጨማሪ የመስህብ ሃብትን ፈጥሮላታል።

የባህር ዳር መለያ የሆነው አገልግልና ሌሎች ባህላዊ ቁሳቁሶች እየተመረተ ወደ ገበያ የሚቀርብባት የእደ ጥበብ ከተማ መሆኗ ሌላው ለጎብኚዎች ምቾት የሚሰጥ ነው። ከጣና የሚወጣው ዓሳና ሌሎች ባህላዊ ምግቧም እንዲሁ።


 

ውቢቷ የባህር ዳር ከተማም የአፍሪካውያንን ችግር በአፍሪካውያን መፍታት ዓላማው አድርጎ የሚካሄደውን 12ኛው የጣና ፎረም ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃ እንግዶችን በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች።

ከጥቅምት 13 - 15 ቀን 2019 ዓ.ም «በአፍሪካ የሰላም መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦፖለቲካ ለውጥ» በሚል መሪ ሐሳብ በሚካሄደው ፎረም ላይ የበርካታ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ምሁራንና ከፍተኛ ባለሙያዎች በአህጉሪቷ መጻኢ ዕድል ላይ በመወያየት ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋሻው እንዳለው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ 12ኛውን የጣና ፎረም ለማዘጋጀት የተለያዩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተከናውነዋል።

ከሪዞርቶችና ሆቴሎች፣ ከሆቴል ባለሙያዎች ማህበር ሥራ አስኪያጆችና ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመምከር ለእንግዶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መሰራቱን አስረድተዋል። 

በሚቆዩበት ጊዜም የጣና ዳርና ከኤርፖርት እስከ ጊዮርጊስ እና አሮጌው የአባይ ድልድይ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የተገነባውን የኮሪደር ልማት ሥራ በመጎብኘት ራሳቸውን እንዲያዝናኑ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

ለእንግዶች የተቀላጠፈ መስተንግዶና አገልግሎት በመስጠት የአገራችንን ገጽታ ከመገንባት ባሻገር የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

በጣና ሐይቅ ለሚንሸራሸሩ እንግዶችም ፈጣን ጀልባዎች ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመው የስጦታ እቃ አቅራቢ ድርጅቶችም አገልግልና ሌሎች የከተማዋ መገለጫ የሆኑ የእጅ ውጤቶችን እንደሚያቀርቡ አስረድተዋል።

የፈለገ ጊዮን ሪዞርት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አይችሉህም ወንድወሰን በሰጡት አስተያየት፤ የጣና ፎረምን ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶችን በአግባቡ ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅት ተደርጓል።

የእንግዶች ማረፊያ ክፍሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ዘመናዊና ፈጣን ጀልባዎች፣ የተሟላ የኢንተርኔት አገልግሎትና የሄሊኮፕተር ማረፊያ ቦታዎችን አዘጋጅተናል ብለዋል።

ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ምሁራንና ባለሙያዎች በከተማዋ ሲንቀሳቀሱም  አገልግሎት የሚያቀርቡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

ጣና ፎረምን ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ በቂ ልምድ አለን ያሉት ደግሞ የብሉ ናይል ሪዞርት ሆቴል የእንግዳ መቀበያ ክፍል ሱፐርቫይዘር አቶ ጌታቸው ይስማው ናቸው።

ሠራተኞችን ቀድመው በማሰልጠን፣ እድሳት የሚያስፈልጋቸውን ክፍሎች በማደስና በመጠገን የእንግዶች ማረፊያ ክፍሎች፣ የመመገቢያ አዳራሾች፣ ባሮችና የመዝናኛ ቦታዎችን ዝግጁ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም