የጣና ፎረም በስኬት እንዲጠናቀቅ የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የጣና ፎረም በስኬት እንዲጠናቀቅ የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል
ባህር ዳር፤ጥቅምት 10/2019(ኢዜአ)፦በባህር ዳር ከተማ የሚካሄደው የጣና ፎረም ያለምንም ችግር በስኬት እንዲጠናቀቅ በፀጥታ ሃይሉ በኩል የተሟላ ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
12ኛው የጣና ፎረም ከጥቅምት 13 እስከ 15 ቀን 2019 ዓ.ም ''በአፍሪካ የሰላም መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦፖለቲካ ለውጥ''በሚል መሪ ሐሳብ በባህር ዳር ከተማ ይካሄዳል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራልና የኦፕሬሽናል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ዘለቀ አለባቸው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ ፎረሙ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ተደርጓል።
የክልሉ የፀጥታ ኃይል ከመከላከያና ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ያደረጉት አስተማማኝ ዝግጅት አህጉር አቀፍ የሆነውን ፎረም በሰላም ለማጠናቀቅ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በቅድመ ዝግጅቱ ወቅት ከተለያዩ የሲቪክ ማኅበራት ከተውጣጡ ወጣቶችና ከጀልባ ማኅበራት ጋር በመወያየት ሰላሙን በጋራ ለመጠበቅ የሚያስችል መግባባት በመፍጠር ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ጋር በአገልግሎት አሰጣጥና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ በመወያየት በፎረሙ ለመሳተፍ ለሚመጡ እንግዶች መልካም መስተንግዶ እንዲያደርጉ መግባባት ተፈጥሯል ብለዋል።
በተጨማሪም እንግዶች ከፎረሙ ጎን ለጎን የጣና ገዳማትና በአካባቢው የሚገኙ የቱሪዝም ቦታዎችን ያለምንም ችግር እንዲጎበኙ የጸጥታ ኃይል ስምሪት መደረጉን ገልጸዋል።
የተደረገው ዝግጅትም በፎረሙ ለመሳተፍ የሚመጡ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን በከተማዋና አካባቢው የሚገኙ ቅርሶችን ተዘዋውረው እንዲጎበኙ በማስቻል የአገራችንን ገጽታ ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
ህብረተሰቡም እንግዶች በሰላም መጥተው በሰላም እስኪመለሱ ድረስ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን የተለመደ ትብብሩንና ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።