ቀጥታ፡

ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናን እያቃለለ የሚገኘው የጤና መድህን አገልግሎት

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ)፦የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ዕለታዊ የገንዘብ እጥረት ሳያሳስባቸው ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ እያገዛቸው መሆኑን የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ገለጹ።

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት በጤናው መስክ ጤናው የተጠበቀ ዜጋን ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶችን ከማገዝ ረገድ ጉልህ አበርክቶ ያለው እንደሆነ ይታወቃል።

የመደመር መንግሥት በ2019 ዓ.ም በማኅበራዊ ዘርፍ ትኩረት ተደርጎባቸው ከሚሰሩ ተግባራት መካከል የዜጎችን የጤና መድህን ሽፋን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ማከናወን ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።

በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ኢዜአ ያነጋገራቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና የሚቀረፍ ነው ብለዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ወይዘሮ ከበቡሽ ከማ የጤና መድህን አገለግሎት መጠቀም ከጀመሩ ከ3 ዓመት በላይ እንደሆናቸው በመጠቆም መንግሥት ባመቻቸው በዚህ መልካም እድል የህክምና ሂደታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ እንደስቻላቸው በመግለጽ አገልግሎቱ ለጤናችን መጠበቅ ዋስትናችን ነው ሲሉም አክለዋል።


 

ሌላኛው በዚሁ ሆስፒታል መድኃኒት ለመግዛት ወረፋ ሲጠባበቁ ያገኘናቸው አቶ ብለሁ አሰፋ በበኩላቸው፤ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚ ከመሆናቸው በፊት የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ይቸገሩ እንደነበር ገልጸው፤ በጤና መድህን የህክምና አገልግሎቶችን ያለምንም ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ነው የተናገሩት።

በህክምና የሚታዘዙላቸውን መድኃኒትም በጤና መድህናቸው ህክምና ባገኙበት ተቋም ወይም ደግሞ መድኃኒት ለመግዛት በተፈቀዱ መድኃኒት ቤቶች ሄደው እንደሚገዙም ጠቁመዋል።

ባለቤታቸው በአንድ ወቅት ባጋጠማቸው ህመም ሳቢያ የጤና መድህን ሽፋን ለማግኘት መመዝገባቸውን በመግለጽ በአሁኑ ወቅት እሳቸውም ህክምና ሲያስፈልጋቸው እየታከሙበት መሆኑን የገለጹት ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ በኸርያ ሻህሪ ናቸው።


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ይመኑ ክብረት በበኩላቸው በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ተመላላሽ ታካሚ መሆናቸውን በመናገር ህክምናቸውን በጤና መድህኑ እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የጤና መድህን አስተባባሪ አሰለፈች ወርቁ በበኩላቸው፤ በሆስፒታሉ ለህክምና አገልግሎት የሚመጡ የጤና መድህን ተገልጋዮች ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ያምሮት አንዷለም፤ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት ሰዎችን የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በተሰራው ስራ 1 ሺህ 272 ወረዳዎች የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽ ተደርገዋል ብለዋል።


 

በዚህም ባለፈው ዓመት ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ሽፋን እንዲያገኙ በማድረግ የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ምህዳር ተፈጥሯል ሲሉ ተናግረዋል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የአባላት ምዝገባና እድሳት ከመስከረም እስከ የካቲት 30 ቀን 2019 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ጊዜያት የሚከናወን ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም መሰረት የዘንድሮ የአባልነት ምዝገባና እድሳት መርሃ ግብር በተጠቀሰው ወራት ዜጎች በወቅቱ በመመዝገብ የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም