በምስራቅ ኦሮሚያ ዞን በዘንድሮው ዓመት ከስድስት ሺህ ቶን በላይ ማር ለማምረት ታቅዷል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ኦሮሚያ ዞን በዘንድሮው ዓመት ከስድስት ሺህ ቶን በላይ ማር ለማምረት ታቅዷል
ጭሮ፣ ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ) ፡-በምስራቅ ኦሮሚያ ዞን የማር ምርት ኢንሼቲቭን በማጠናከር በዘንድሮው ዓመት ከስድስት ሺህ ቶን በላይ ማር ለማምረት የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
በዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት የማር ልማት ስራ አስተባባሪ አቶ ዳኛቸው ተረፈ እንዳሉት የማር ምርትን ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
በዚህም በተቀረጸው ኢኒሼቲቭ አማካኝነት ዘመናዊ ቀፎዎችን የማሰራጨት፣ የንብ አናቢዎችን አቅም የማጎልበትና ለልማቱ ምቹ የሆነ የተፈጥሮ አካባቢ የመፍጠር ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በዚህ ዓመትም በዞኑ የዶባ፣ ጡሎ፣ ሀብሮ፣ ኦዳቡልቱምን ጨምሮ በተመሳሳይ አካባቢ በሚገኙ አስራ አምስት ወረዳዎች 68 ሺህ 503 ዘመናዊ ቀፎዎችን ለማሰራጨት ታቅዶ እስካሁን ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ ቀፎዎች በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶአደሮች መሰራጨታቸውን አመልክተዋል።
በዚህ ዓመት ለአርሶ አደሮቹ ለማሰራጨት የታቀደው ዘመናዊ ቀፎ ካለፈው ዓመት ከ10ሺህ በላይ ብልጫ እንዳለው ገልፀዋል።
ኢንሼቲቩ ከመጀመሩ ከሦስት ዓመት በፊት በየዓመቱ ይሰራጭ የነበረው ዘመናዊ ቀፎ ከ500 የማይበልጥ እንደነበር የገለፁ ሲሆን፣ አሁን ላይ የቀፎ ስርጭቱ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉ በኢንሼቲቩ የተገኘ እመርታ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም በዓመቱ ስድስት ሺህ 100 ቶን ማር ለማምረት መታቀዱንና ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በሁለት ሺህ ቶን ብልጫ ያለው መሆኑን ገልፀዋል።
በየዓመቱ እያያደገ ያለው ምርታማነት የዘመናዊ ቀፎ ስርጭትን፣ የንብ አናቢዎችን የምርት አቅም ማሳደግንና የንብ ማነብ ሥራን ማዘመንን በማጠናከር የማር ምርትን ለማሳደግ በመሰራቱ እንደሆነ አብራርተዋል።
የማር ምርት ኢንሼቲቩን ለመደገፍም እያንዳንዱ ወረዳ 14 ሚሊዮን ብር በጀት መያዙን ገልፀው፤ ይህም ለኢንሼቲቩ የሚያስፈልጉ የድጋፍ ሥራዎችን ለማስፈጸምና የንብ አናቢዎችን የምርት አቅም ለማጠናከር የሚውል መሆኑን ተናግረዋል።
ኢንሼቲቩ ዘመናዊ ቀፎዎችን ከማሰራጨት ባለፈ የንቦችን ቤት የመሥራት፣ ለንብ አናቢዎች ስልጠና የመስጠትና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን ለንብ ማነብ ምቹ በሆነ መልኩ የማከናወን ተግባራትን ያካትታል ብለዋል።
የኢንሼቲቩ ተጠቃሚ የሆኑ አርሶ አደሮች ዘመናዊ ቀፎዎችን የሚያገኙት የእጅ ዋጋ ብቻ 1ሺህ 500 ብር በመክፈል መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም አርሶ አደሮች ወደ ዘመናዊ የንብ ማነብ ሥራ እንዲገቡ፣ የምርት አቅማቸውን እንዲያሳድጉና ከማር ምርት የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አስታውቀዋል።
በዞኑ የሸነን ዱጎ ወረዳ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት የማር ልማት ስራ አስተባባሪ አቶ አስናቀ ተሾመ እንዳሉት በወረዳው የማር ልማት ኢንሼቲቭ ከተጀመረ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ከስድስት ሺህ በላይ ዘመናዊ ቀፎዎች በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶአደሮች ተሰራጭተዋል።
በዚህ ዓመትም አርሶአደሩ በመስኩ እንዲሰማራ የዘመናዊ ቀፎ ስርጭት ካለፈው ዓመት በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።