የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን ለቀጣናዊ የጋራ ብልጽግና መረጋገጥ ወሳኝ ነው-ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን ለቀጣናዊ የጋራ ብልጽግና መረጋገጥ ወሳኝ ነው-ምሁራን
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን ለቀጣናዊ የጋራ ብልጽግና መረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው ምሁራን ገለጹ።
የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ የተጀመረው ጥረትና የሄደበት ምዕራፍ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያሳየ ይገኛል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የኢትዮጵያን ፍትሐዊ ጥያቄ በመገንዘብ ተገቢውን ድጋፍና ትኩረት እየሰጠው ይገኛል።
የሎጂስቲክስ ዘርፍ ተመራማሪው ተመስገን ዋለልኝ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የባህር በር የሀገራትን የንግድ እንቅስቃሴ፣ የምርት ማጓጓዣና የዓለም ገበያ ትስስር በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤት አለመሆኗ ምርቶችን በወቅቱና በተወዳዳሪ ዋጋ ወደ ዓለም ገበያ ለማቅረብ ተጨማሪ የሎጂስቲክስ ወጪዎችንና ጫናዎችን እያስከተለባት እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
እነዚህ ተጨማሪ ወጪዎች በውጭ ንግድ ላይ ብቻ ሳይሆን ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ሸቀጦች ላይም የዋጋ ጭማሪ በማስከተል በሸማቾች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄዋን ከጂኦግራፊያዊና ከሕዝብ ቁጥር እድገቷ ባሻገር ከታሪካዊ፣ ህጋዊ እና የረጅም ጊዜ ልማት አንጻር ማቅረቧ ተገቢ መሆኑን አብራርተዋል።
የወደብ አገልግሎትን በብቃት ማስተዳደር የሀገርን የንግድ ደኅንነትና የአቅርቦት ሰንሰለት ጽናት ለማረጋገጥ ወሳኝ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል።
ሀገሪቱ ይህን ጥያቄዋን ለማሳካት የሰላማዊ ዲፕሎማሲን፣የጋራ ተጠቃሚነትንና የሰጥቶ መቀበል መርህን በመከተል ከጎረቤት ሀገራት ጋር እየተሠራ መሆኑ አበረታች ነው ብለዋል።
ይህም የኢትዮጵያን የንግድና የኢኮኖሚ አቅም ከማጠናከሩ ባሻገር የቀጣናውን ዘላቂ ሰላም እና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማጎልበት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።
በአጠቃላይ ጥያቄው ከአሁናዊ የኢኮኖሚ ፍላጎት ባለፈ የሀገርን የወደፊት ስትራቴጂካዊ ህልውና መሠረት ያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ረገድ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው የተናገሩት ደግሞ የኢኮኖሚ ባለሙያው ነሞምሳ መንገሻ ናቸው።
ይህም አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን በማቀላጠፍ በእያንዳንዱ ዜጋ ሕይወት ላይ የሚፈጥረውን ጫና ለመቀነስ ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
በመሆኑም የባሕር በር ማግኘት የሀገሪቱን የረጅም ጊዜ የልማት ግቦች ለማሳካትና የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል መሠረታዊ መፍትሔ መሆኑን ጠቁመዋል።