ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ) ፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ከቀኑ 9 ሰዓት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሸገር ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ከሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ያገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአንድ ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ተጋጣሚው ሸገር ከተማ በአራት ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ጨዋታው ኢትዮ ኤሌከትሪክ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ለማግኘት፣ ሸገር ከተማ ከሁለተኛ ሳምንት የአቻ ውጤት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።

በሌላኛው መርሐ ግብር ሀላባ ከተማ ከፋሲል ከነማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በሀላባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

አዲስ አዳጊው ሀላባ ከተማ ከሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥብ በማግኘት ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ያለው ፋሲል ከነማ በአንድ ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

ሀላባ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባል።

ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ለማግኘት ይፋለማል።

የሶስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር እስከ ጥቅምት 12 ቀን 2019 ዓ.ም ይቆያል።

በሶስተኛ ሳምንት ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከባህር ዳር ከተማ፣  ሲዳማ ቡና ከሃዋሳ ከተማ ሊያደርጓቸው የነበሩ ጨዋታዎች በአህጉራዊ ጨዋታዎች ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፈዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሊጉን በስድስት ነጥብ እየመራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም