ፒኤስጂ ከባርሴሎና -ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው ታላቅ ፍልሚያ - ኢዜአ አማርኛ
ፒኤስጂ ከባርሴሎና -ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው ታላቅ ፍልሚያ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ)፦ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሶስተኛ ዙር መርሐ ግብር ዛሬ ይጀመራል።
ምሽት አራት ሰዓት ላይ ፒኤስጂ ከባርሴሎና በፓርክ ደ ፕሪንስ የሚያደርጉት ጨዋታ የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ ስቧል።
ያለፉት ሁለት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎች ባለቤት ፒኤስጂ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ያደረጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ በስድስት ነጥብ የሊግ ምዕራፉን እየመራ ይገኛል።
የአምስት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ባርሴሎና በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ ብዙ ጎል ባገባ በሚለው መለያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በሁለቱ ጨዋታዎች ላይ ፒኤስጂ 10፣ ባርሴሎና ደግሞ ዘጠኝ ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ይህ አሃዝ ሁለቱ ክለቦች ያላቸውን የማጥቃት ብቃት የሚያሳይ ነው።
ሁለቱ ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሲገናኙ የአሁኑ ለ16ተኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 15 ጨዋታዎች ባርሴሎና በስድስቱ ድል ሲቀናው ፒኤስጂ አምስት ጊዜ አሸንፏል። በቀሪ አራት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
በ15ቱ ጨዋታዎች ላይ ባርሴሎና 29 ግቦችን ሲያስቆጥር ፒኤስጂ 28 ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ቡድኖቹ ለመጨረሻ ጊዜ እ.አ.አ በ2025/26 የውድድር ዓመት በተገናኙበት ጨዋታ ፒኤስጂ 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ኡስማን ዴምቤሌ፣ ዴዚሪ ዱዌ እና ክቪቻ ክቫራትስኬሊያ ከፒኤስጂ እንዲሁም ራፊኒሃ፣ ላሚን ያማል እና አንቶኒ ጎርደን ከባርሴሎና የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።
የሁለቱ ድንቅ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለተመልካቾች ትልቅ ጉጉትን ፈጥሯል።
ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ማንችስተር ሲቲ ከኤኢኬ አቴንስ፣ ሊቨርፑል ከቪያሪያል፣ ናፖሊ ከቦዶ ግሊምት፣ ስቱትጋርት ከአትሌቲኮ ማድሪድ፣ ፖርቶ ከፒኤስቪ አይንድሆቨን እና ሮማ ከስሎቫን ብራቲስላቫ በተመሳሳይ ምሽት አራት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ምሽት 1 ሰዓት ከ45 ሳባህ ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ እና ፌነርባቼ ከስላቪያ ፕራግ ይጫወታሉ።