ቀጥታ፡

ሕወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት አፍርሶ ለሌላ ዙር ጦርነት ሲዘጋጅ ነበር- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2019 (ኢዜአ):- ሕወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት አፍርሶ ለሌላ ዙር ጦርነት ሲዘጋጅ መቆየቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በትግርኛ ቋንቋ ቆይታ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው እንዳመለከቱት፣ በጥቅምት 2015 ዓ.ም የተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት በህወሃት ቡድን ፈርሷል።

የፕሪቶሪያ ስምምነት ቁልፍ ይዘቶች ተኩስ ማቆም፣ ሁሉንም ዓይነት አገልግሎቶች መመለስ፣ ትጥቅ ማስፈታት፣ ተፈናቃዮችን መመለስ እና ለሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱ እውቅና መስጠት እንደነበሩ አውስተው በፌደራል መንግስት በኩል የሚቻለውንና የሚጠበቀው ሁሉ መፈጸሙን አብራርተዋል።

ሕወሓት ስምምነቱን ከመተግበር ይልቅ በተቃራኒው ይሰራ እንደነበርና ትጥቅ ከመፍታት ይልቅ ወደ መሳሪያ ግዢና ልመና በመግባት፣ በግልጽ ወጣቶችን በመመልመል ለሌላ ዙር ጦርነት ሲዘጋጅ እንደነበር ገልጸዋል።

ከሁሉ በላይ ደግሞ ከስምምነቱ በኋላ ሕወሓት ተፈናቃዮችን እንደ መያዣ በማድረግ ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ ማድረጉን፤ በተጨማሪም በፌደራል መንግስት ዳግም አገልግሎት እንዲሰጡ የተደረጉትን እንደ አየር መንገድ፣ ባንክ እና ቴሌኮምን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶችን የማፍረስና የመዝጋት ተግባር መፈጸሙን አመልክተዋል።

ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ ጦርነት አያዋጣም፤ ይቅርብን፣ ሰላም ይሻላል ብለን መክረናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሕወሓት ግን ምክሩን ቸል በማለት ከተለያዩ ኃይሎች ጋር በመተባበር አላስፈላጊ ጦርነት በማወጅ የፕሪቶሪያን ስምምነት አፍርሶታል ብለዋል።

በሕወሓት ምክንያት በሚፈጠረው ጦርነት በሕዝብ ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷልም ነው ያሉት።

በመሰረቱ ጦርነት መጥፎ ነው፣ ምንም ጥቅም የለውም፤ ከሁሉ በላይ ለውጭ ኃይሎች ጥቅም ሲባል የሚደረግ ጦርነት ደግሞ የበለጠ የከፋ ነው ብለዋል።

የስነ-ልቦናዊ ጉዳቱም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤ በልማትና በኢኮኖሚውም ላይም ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል።

ስለሆነም ክላሽንኮቭ ተሸክሞ የሚዞረው ወጣት ወደ ሥራው ተመልሶ በትግራይ ልማት እና ማገገም ላይ መሳተፍ እንዳለበት አመልክተዋል።

ብዙ ወጣት በኃይል ተገዶ መሰለፉን ጠቅሰው የተመለሱት እንደተጠበቁ ሆነው ያልተመለሱት ወጣቶች እንዲመለሱ መክረዋል።

የሕወሓት መሪዎች ለ50 ዓመታት ጦርነት ሲከፍቱ አልሞቱም፣ አልቆሰሉም፤ ልጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውንም ወደ ውጭ ሀገርና አዲስ አበባ በመላክ በንግድና ሕንፃ ስራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ ብለዋል።

የትግራይ ወጣት መኖርና ሕይወቱን መለወጥ አለበት እንጂ ለነሱ ብሎ መሞትና መቁሰል የለበትም ሲሉ ገልጸዋል።

የትግራይ ወጣት እንዳይቆስልና እንዳይደክም፤ አካሉንና አእምሮውን ለልማት ማዋል እንዳለበት መክረዋል።

ወጣቱ ውሎውን በዩኒቨርሲቲ፣ በንግድ፣ በግብርናና በፋብሪካዎች ውስጥ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

እጅህ ቃታ ከመሳብ ይልቅ በኮምፒውተር ላይ መዋል አለበት፤ ክላሽንኮቭህን አውርደህ ወደ ልማትህ ተመለስ ሲሉም መክረዋል።

ሕወሓት መርህ የለውም፤ በአፍ ሕዝባዊ ይመስላል፣ በተግባሩ ግን ፀረ-ሕዝብ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕወሓት ከፀረ-ሕዝቦች ጋር ስለተባበረ የሚያመጣው ለውጥ የለም። ታግዬ አመጣሁት የሚለውን ሕገ-መንግስት ለማፍረስ ሕገ-መንግስቱን ከማይቀበሉ ኃይሎች ጋር ተባብሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም