የትግራይ ሕዝብ በህወሓት ምክንያት እጅግ ብዙ ዋጋ ከፍሏል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ሕዝብ በህወሓት ምክንያት እጅግ ብዙ ዋጋ ከፍሏል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2019 (ኢዜአ):- የትግራይ ህዝብ በህወሓት ምክንያት እጅግ ብዙ ዋጋ መክፈሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በትግርኛ ቋንቋ ቆይታ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው ህወሓት ቅንጣት ያክል የትግራዋይነት ባህሪ የሌለው መሆኑን እና የመረጠው አመለካከት እንዲሁም የተከተለው ፖሊሲና እምነት ከትግራይ ሕዝብ ክብር ጋር ፈጽሞ የማይሄድ መሆኑን አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም፣ የአንድን የፖለቲካ ድርጅት ህልውና ከሕዝብ ህልውና ጋር ማያያዝ፣ ወይም የሕዝብን ደህንነት ከድርጅት ጋር ማቆራኘት ፍጹም መሰረት የሌለው እና ከስሕተትም አልፎ አደገኛ አስተሳሰብ ነው ብለዋል።
እንዲህ ያለው አካሄድ የሕዝብን ህልውና በቀጥታ አደጋ ውስጥ እንደሚጥል ተናግረዋል።
ህወሓት 50 ዓመታት ገደማ የሆነው ድርጅት መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የትግራይ ሕዝብ ግን ለሺዎች ዓመታት የኖረ እና በቀጣይም ለሺዎች ዓመታት የሚኖር ሕዝብ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ህወሓት ከሃምሳ ዓመት በፊት አልነበረም፤ አሁንም ታሪክ እየሆነ መሆኑን ነው የገለጹት።
ከትግራይ ወጥቶ ኢትዮጵያን መምራት አዲስ ክስተት እንዳልሆነ እና ቀደም ሲልም እንደ አጼ ዮሐንስ ያሉ መሪዎች ከዛው ወጥተው ሀገር መምራታቸውን አስታውሰዋል።
እነሱም ዛሬ የሉም፤ ነገር ግን የትግራይ ሕዝብ አለ፤ ህወሓትም እየከሰመ ይገኛል፣ ሕዝቡ ግን ይቀጥላል ብለዋል።
መሪዎችና የፖለቲካ ድርጅቶች ይነሳሉ ይወድቃሉ፣ መንግስታትም ይለዋወጣሉ፤ ሕዝብና ሀገር ግን ይቀጥላሉ ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የህወሓት ዕድሜ አጭር መሆኑን እና ወደ ኋላ ተመልሶ ሲታይም የትግራዋይነት መዓዛ እንዳልነበረው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ምንም እንኳን በድርጅቱ ውስጥ የተሰለፉት አብዛኞቹ አባላት ተጋሩ ቢሆኑም እና ድርጅቱ በትግራይ ውስጥ የቆየ ቢሆንም፣ የድርጅቱ አመለካከት ግን ከትግራይ ሕዝብ ክብር ጋር የሚስማማ እንዳልሆነ አመልክተዋል።
የትግራይ ሕዝብ በህወሓት ምክንያት እጅግ ብዙ ዋጋ የከፈለ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ይህ እውነታም በግልጽ እየታየ ነው ብለዋል።
የትግራይ ሕዝብ እንደ ቀደመው ጊዜ ሁሉ ራሱን ችሎ እንደሚቀጥል እና በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥም እንደወትሮው የድርሻውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።