በኮሚሽኑ የሀዋሳ ቅርንጫፍ በቴክኖሎጂ የታገዘ ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኮሚሽኑ የሀዋሳ ቅርንጫፍ በቴክኖሎጂ የታገዘ ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ ነው
ሀዋሳ፣ ጥቅምት 9/2019 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በቴክኖሎጂ የታገዘ ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠቱ በስራቸው ላይ ውጤታማ እንዳደረጋቸው ደንበኞች ገለጹ።
በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከአምራቾች፣ አስመጪዎች፣ ላኪዎችና ከጉምሩክ አስተላላፊዎች ጋር በሀዋሳ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ቶዮ ሶላር ማኑፋክቸርንግ ካምፓኒ ሎጂስቲክስ ሃላፊ ጋዲሴ ገመቹ እና የእኛ እርሻ መሳሪያዎች ማምረቻ ድርጅት የመጡት አቶ ደረጀ አንበስ፤ ኮሚሽኑ በዲጅታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት መስጠቱ ፈጣን፣ የተቀላጠፈና ግልጽ አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል ብለዋል።
በኮሚሽኑ በገቢ እና ወጪ ንግድ ላይ ከዚህ ቀደም የነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ የተንዛዛ እንደነበረ አስታውሰው አሁን ላይ መሻሻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት መጀመሩ ጊዜና ጉልበትን ከመቆጠብ ባለፈ ብልሹ አሰራሮችን በመግታቱ በስራቸው ላይ ውጤታማ እንዳደረጋቸው ጠቁመው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
የፔቭ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሃላፊነቱ የግል ድርጅት የጉምሩክ አስተላላፊ አቶ ዳዊት ሰለሞን እና የአማ ቢዝነስ ግሩፕ ማህበራዊ ጉዳዮችና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ታደሰ አባተ፤ ኮሚሽኑ በገቢም ሆነ በወጪ ዕቃዎች አገልግሎት ቀልጣፋ መስተንግዶ እየሰጠ በመሆኑ አመስግነው አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኬያጅ አቶ ታደሰ መርዕድ፤ የሀዋሳ ኢኮኖሚ ዞንን ጨምሮ የወጪና ገቢ ንግድን ሊያሳልጥ የሚችልና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ የሚያግዝ የጉምሩክ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘርፉ የነበሩ ማነቆዎችን ለመፍታት የሚያስችል ዘመናዊ አሰራር በመዘርጋት ወደ ስራ በመግባት ውጤታማ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።
በባለፈው በጀት ዓመት ከ4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ ያሳካው የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ 6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ አቀዶ እየሰራ መሆኑ ታውቋል።