ቀጥታ፡

የሙስና ተጋላጭነትን ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመረው ቅንጅታዊ አሰራር ይጠናከራል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2019 (ኢዜአ)፦ የሙስና ተጋላጭነትን ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመረው ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረዲ ገለፁ።

ኮሚሽኑ የተቋማት የሙስና ተጋላጭነትን መቀነስ እና ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር ያለመ የውይይት እና የስራ ስምምነት መርሃ ግብር አካሄዷል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ኦዲተር፣ የኮሙኒኬሽን ቢሮ፣ የፖሊስ ዋና መምሪያ ጨምሮ የበርካታ ባለድርሻ አካላት እና ተቋማት ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረዲ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ሙስና ዘር፣ እድሜ እና አካባቢ ሳይለይ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን የሚጎዳ ተግባር ነው።

በዚህም ሙስናን መከላከል የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ሀላፊነት ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የፀረ-ሙስና ስራዎች ትውልዱን በስነ-ምግባር የመቅረጽ፣ አሰራሮችን ግልጽ የማድረግ እና የሙስና ተጋላጭነትን የመቀነስ አዎንታዊ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልፀዋል።

በቀጣይም የሚሰሩ ስራዎችም ሙስና ከተፈጸመ በኋላ ሀብት ማስመለስ እና ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ብቻ ሳይሆን፣ ወንጀሉ አስቀድሞ እንዳይፈጸም መከላከል ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የሙስና ተጋላጭነትን ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመረው ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ተቋማት ተቀናጅተው ወደ ስራ መግባታቸው ሙስናን ለመከላከል ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የመከላከል ስራዎችን እና ግብረ-ገብነትን ለማጠናከር ከተጋላጭነት ክፍተቶች በመነሳት አጥፊዎች ላይ ተመጣጣኝ ህጋዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እና ሂደቱ በግንባር ቀደምትነት በሁሉም ባለድርሻ አካላት መመራት እንዳለበት ጠቅሰዋል።

የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ጥላሁን ካሳ በበኩላቸው፤ የሙስና ተጋላጭነትን ለመቀነስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም