የመደመር መንግስት ለሰላምና ለዘላቂ ልማት የያዘው ግብ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት መሰረት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግስት ለሰላምና ለዘላቂ ልማት የያዘው ግብ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት መሰረት ነው
ሆሳዕና፤ጥቅምት 9/2019 (ኢዜአ)፡-የመደመር መንግስት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ ሀገራዊ ልማትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የያዘው ግብ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን ገለጹ።
ምሁራኑ ዜጎች ሰላምን በማጽናት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባም አመልክተዋል።
ኢዜአ ካነጋገራቸው ምሁራን መካከል በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ጌታሁን አበራ እንዳሉት፣ የመደመር መንግስት ከግጭት ይልቅ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ቁርጠኝነቱን አሳይቷል።
ይህም እንደ ሀገር የመነጋገር ባህልን ከማሳደግ ባለፈ ሀገራዊ ልማትን በዘላቂነት በማረጋገጥ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል በነበሩ መንግስታት ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴና የመነጋገር ባህል ባለመዳበሩ ልዩነቶችን በኃይል ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ጎልቶ ይታይ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይህም ልዩነትን በማስፋት የዴሞክራሲ ምህዳሩን አጥቦት ቆይቷል ያሉት መምህር ጌታሁን፣ በአሁኑ ወቅት በየደረጃው ህዝብን በማሳተፍ የሚከናወኑ ተግባራት መተማመንን ያጠናክራሉ ብለዋል።
በመንግስት ሰላምን በማጽናትና የውይይት ባህልን በማዳበር ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ህዝቡም የራሱ አጀንዳ በማድረግ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።
እንደ መምህር ጌታሁን ገለጻ፣ መንግስት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ ችግሮችን ለመፍታት አካታችና አሳታፊ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በፓርላማ ጭምር ሀገራዊ ተሳትፏቸው እንዲጎለብት አድርጓል።
ብሔራዊ ጥቅሟ የተጠበቀ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት መንግስት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተደጋጋሚ ማሳየቱን አስታውሰው፣ ጠብመንጃ አንስተው በጫካ ያሉ አካላትም ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመጡ አመልክተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሰላምና ደህንነት ትምህርት መምህርና ተመራማሪው ተመስገን ቶማስ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፣ ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅንና ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር የሁሉም ዜጋ ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን ይገባል።
የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት በርካታ ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙትም ለፈተናዎች ሳይበገር ዛሬ ላይ መድረሱ ዜጎች ለሀገራቸው ያላቸውን ቀናኢነት እና ፍቅርን ያሳያል ብለዋል።
ፈተናዎችን በጽናት ከመሻገር ባለፈ ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ባደረገና በትብብር ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ባህል ግንባታ እየዳበረ መምጣቱን ምሁሩ አስረድተዋል።
ሰላምና ልማት ተነጣጥለው እንደማይታዩና የተሳሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ተመስገን (ዶ/ር)፣ ከድህነት ወጥቶ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።
በሀገር ደረጃ የተጀመሩ ሁሉን አቀፍ የለውጥ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የመደመር መንግስት ቅድሚያ ለሰላም መስጠቱ ተገቢ መሆኑንም ገልጸዋል።