ኢትዮጵያ በስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ዘርፍ ግንባር ቀደም በመሆን እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ዘርፍ ግንባር ቀደም በመሆን እየሰራች ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ዘርፍ በግንባር ቀደምትነት እየሰራች መሆኑን በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የጂኦ-ስፓሻል መረጃ አስተዳደር ክፍል ኃላፊ አንድሬ ኖንጉዌማ ገለጹ።
የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የጂኦስፓሻል መረጃ አስተዳደር 12ኛ ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ጉባዔው ከዛሬ ጥቅምት 9ቀን 2019ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን የጂኦስፓሻል መሪዎችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችንና የልማት አጋሮችን የሚሳተፉበት ይሆናል።
ጉባዔው በአፍሪካ የጂኦስፓሻል መረጃ አስተዳደር ዘላቂ የፋይናንስ አቅርቦትና ፈጠራ ላይ የሚመክርም ሲሆን
በዛሬው ዕለት የቅድመ ጉባዔ መድረክ ተካሂዷል።
በዚህ ወቅት በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የጂኦ-ስፓሻል መረጃ አስተዳደር ክፍል ኃላፊ አንድሬ ኖንጉዌማ እንዳሉት ጉባዔው አባል ሀገራት ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር በጋራ የሚመካከሩበት መድረክ የሚፈጥር ነው።
ሀገራት ልምድ በመለዋወጥና እርስ በርስ መማር የጋራ መፍትሔዎችንና አማራጮችን ለማዘጋጀት የሚረዳ ነውም ብለዋል።
አፍሪካ በጂኦስፓሻል መረጃ ዓለም አቀፍ አዝማሚያዎችን በመገምገም ተወዳዳሪ ሆና እንድትቀጥል ማድረግ መሆኑንም ገልጸዋል።
የጂኦስፓሻል መረጃ እንደ መንገድ፣ ግድብና ትምህርት ቤት ግንባታ አስፈላጊ የሆነ መሠረተ ልማት ከመሆኑም በላይ ለእያንዳንዱ የመሠረተ ልማት ግንባታ የጂኦስፓሻል መረጃ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
የጂኦስፓሻል መረጃ ለዕለት ተዕለት የህይወት ተግባራችን የሚጠቅምና የተባበሩት መንግሥታት አጀንዳ 2030ንና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽንን አጀንዳ 2063 ለመተግበር እገዛ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ የስፔስ አቅም በማልማት ግንባር ቀደምት ሆና በዘርፉ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው የመሬት ምልከታ ሳተላይትን ማምጠቋን አንስተዋል።
ለአባል አገራት፣ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለውሳኔ ሰጪዎች የጂኦስፓሻል መረጃን እንደሌሎች መሠረተ ልማቶች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ትክክለኛ መረጃ ለዕቅድ ዝግጅት፣ ለልማት ስራዎችና ክትትል ለማድረግ ወሳኝ በመሆኑ ይህን በመገንዘብ መስራት ይጠይቃልም ብለዋል።