ቀጥታ፡

አፍሪካ በጣና ፎረም በዕውቀት ላይ የተመሰረቱ ስትራቴጂዎችንና አካታች የመፍትሔ ሐሳቦችን የማፍለቅ አቅሟን እያጎለበተች ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2019 (ኢዜአ)፦አፍሪካ በጣና ፎረም በዕውቀት ላይ የተመሰረቱ ስትራቴጂዎችንና ለአህጉራዊ ችግሮች አካታች የመፍትሔ ሐሳቦችን የማፍለቅ አቅሟን እያጎለበተች መሆኑን አምባሳደሮች ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማዕከል በማድረግ የሚዘጋጀው የጣና ፎረም ለ15 ዓመታት በስኬት ተካሂዷል።

12ኛው የዘንድሮው የጣና ፎረም ''አፍሪካን ወደ ሰላም የሚወስዱ መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የቀጣናዊ ፖለቲካዊ ሽግግር” በሚል መሪ ሐሳብ የፊታችን አርብ በባሕር ዳር ከተማ መካሄድ ይጀምራል።

በኢትዮጵያ የጋና አምባሳደር ማካሪዮስ አካንቢናብ አካንቦ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ጣና ፎረም በአፍሪካ ቀዳሚው የፖሊሲ ጥናት ተቋም መድረክ ነው።

በዓለም ላይ የሙኒክ ፎረም፣ የፓሪስ ደኅንነት ፎረምና ሌሎች በርካታ የሰላምና ደኅንነት ፎረሞች ቢኖሩም፣ አፍሪካ እንደ ጣና ፎረም ያለ መደበኛ ያልሆነ መድረክ ለመፍጠር ብዙ ተጉዛለች ብለዋል።

የጣና ፎረምም የአፍሪካ የግጭት፣ አለመረጋጋት፣ የደኅንነት ሥጋትና የኢኮኖሚ ቀውስ በአህጉራዊ ችግሮችን በአህጉራዊ መፍትሔ ምላሽ የሚሰጡ ሃሳቦችን ማመንጨት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

አህጉራዊ የሰላምና ደኅንነት ፎረሞችን በቀጣናዊ ትብብር ገቢራዊ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው፣ ቀጣናዊ የፋይናንስ አቅም የውይይት አቅምን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ የቡሩንዲ አምባሳደር ዊሊ ኒያምትዌ፤ የጣና ፎረም የአፍሪካ ሕብረት በ2030 የጥይት ድመፅ የማይሰማባት አፍሪካን እውን ለማድረግ የጀመረውን ጥረት እንደሚደግፍ ገልጸዋል።

የጣና ፎረም የሀገር መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የፖሊሲ ጥናት ተቋማት፣ ምሁራንና የቀድሞ መሪዎች የሚሳተፉበት ትልቅ መድረክ መሆኑን ገልጸው፣ በትብብር ለሰላም ዘብ መቆም ይኖርብናል ብለዋል።

የአፍሪካን ሰላምና ደኅንነት ሳናስጠብቅ አህጉራዊ ልማትን ማሳካት አንችልም ያሉት አምባሳደሩ፤ አህጉራዊ ሥጋቶችን በአህጉራዊ ውይይትና ትብብር ለመፍታት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ የኬንያ ኤምባሲ ተልዕኮ ምክትል ኃላፊ ፔትሮኒላ ዌር በበኩላቸው፤ ኬንያ በጣና ፎረም ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆኗን ገልጸዋል።

ኬንያ በተለያዩ ጊዜያት የገጠሟትን ግጭቶች የውጭ ጣልቃ ገብነት ሳያስፈልጋት በራሷ አቅም የመፍታት ልምድ እንዳላት ገልጸው፣ ከዚህ አኳያ የጣና ፎረም ወሳኝ መድረክ ነው ብለዋል።

የጣና ፎረም አፍሪካውያን በእውቀትና በመረጃ ላይ ተመስርተው ትክክለኛ የፖሊሲ አማራጮችን ማውጣት የሚችሉበትን አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም