አዲሱ አስተዳደር የተለማቸውን ሁለንተናዊ የልማት ትልሞች ለማሳካት የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ አስተዳደር የተለማቸውን ሁለንተናዊ የልማት ትልሞች ለማሳካት የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን
ድሬደዋ፣ ጥቅምት 9/2019(ኢዜአ)፡- አዲሱ የድሬዳዋ አስተዳደር ያቀዳቸውን ሁለንተናዊ የልማት ዕቅዶች ለማሳካት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የብየአዋሌ ገጠር ክላስተር ነዋሪዎች ገለጹ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከተረጂነት ወደ አምራችነት የመሸጋገር ጉዞን ለማፋጠን በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከብየአዋሌ ገጠር ክላስተር ነዋሪዎች ጋር ውይይት አካሄዷል።
ነዋሪዎቹ በውይይቱ ወቅት አዲሱ የድሬዳዋ አስተዳደር ያቀዳቸውን ሁለንተናዊ የልማት ዕቅዶች ለማሳካት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ አክለውም የአነስተኛ መስኖ ፕሮጀክቶች እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ሊጠናከሩ እንደሚገባም አንስተዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል ሼህ አሚን አሊ እና አቶ መሐመድ አብደላ እንዳሉት፤ ባለፉት 5 ዓመታት መንግስት በወሰደው ቁርጠኝነት የገጠሩን ማህበረሰብ የአነስተኛ መስኖና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ በማድረግ ከተረጂነት እንዲወጣ ተሠርቷል።
በተለይ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና በተፋሰስ ልማት የተከናወኑ ተግባራት የከርሰ ምድር ውሃ እንዲጨምር በማስቻሉ፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ታግዘው የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማምረት ገቢያቸውን ማሳደጋቸውን ተናግረዋል።
ክላስተሩ ለፍራፍሬና ለአትክልት ልማት ምቹ በመሆኑ ከተረጂነት ወደ አምራችነት የመሸጋገሩን ጉዞ ለማፋጠን እያገዘ ይገኛል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አሚና አህመድ እና ወይዘሮ አሻ አሊ ናቸው።
እነዚህን ጅምር ሥራዎች ይበልጥ ለማሳደግ አዲሱ አስተዳደር ውሃ ገብ ለሆኑ ቀበሌዎች የአነስተኛ መስኖና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ማሳደግ እንዳለበት ገልጸዋል።
ወጣት አብዲ ዑመር በበኩሉ፣ የገጠሩ አካባቢ ወጣቶችን በሥራ እድል ተጠቃሚ ማድረጉ ላይ በትኩረት ሊሠራ የሚገባው ሥራ አለ ብሏል።
ውይይቱን የመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አብዱላሂ አደን ለተነሱ ሐሳቦች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፣ አስተዳደሩ የገጠሩን ህብረተሰብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል አረጋግጠዋል።
ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ አበረታች ሥራዎች ልዩ ስትራቴጂ በመንደፍ በላቀ ደረጃ እንደሚቀጥሉም አክለዋል።
በገጠሩ ክፍል የሚስተዋሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ቅደም ተከተል በመስጠት ለመፍታት የተቀናጀ ሥራ እንደሚሠራ አንስተው መሰል የውይይት መድረኮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ገጠር ቀበሌዎች ከ94 በመቶ በላይ የሚሆነውን መልክዓ ምድር የሚሸፍኑ ሲሆን፣ የማህበረሰብ ስብጥሩም አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች መሆናቸው ይታወቃል።
ዝናብ አጠር በሆነው በዚህ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ነዋሪዎች ለዘመናት የተጫናቸውን የተረጂነት እሳቤ በመስበር ወደ አምራችነት በመሸጋገር በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን እያረጋገጡ ይገኛሉ።