የመደመር መንግስት የልማት እቅዶች ከግብ እንዲደርሱ ድጋፋችንን እናጠናክራለን-የቀቤና ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግስት የልማት እቅዶች ከግብ እንዲደርሱ ድጋፋችንን እናጠናክራለን-የቀቤና ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች
ወልቂጤ፤ ጥቅምት 9/2019 (ኢዜአ)፡-በመደመር መንግስት የተቀየሱ የልማት እቅዶች ከግብ እንዲደርሱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የቀቤና ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት በቀጣይ ለማከናወን በያዛቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅዶች ላይ ከልዩ ወረዳው ነዋሪዎች ጋር ዛሬ በወልቂጤ ከተማ መክሯል።
በምክክር መድረኩ ላይ አስተያየት የሰጡ የቀቤና ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች፤ የመደመር መንግስት የዜጎችን ሁለተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው የልማት ግቦች እንዲሳኩ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ሃጅ ሃሰን ኑጋ መንግስት የነደፋቸው የልማት እቅዶች እንዲሳኩ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
በልዩ ወረዳው የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለመዘርጋት የተያዘው ዕቅድ የሚበረታታና በተለይ የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሂክማ ጀማል በበኩላቸው የመደመር መንግሥት የያዛቸው የልማት ግቦች የህዝቡን ህይወት የሚቀይር እና ሰላምን የሚያፀና መሆኑን ጠቁመዋል።
በወረዳው የአካባቢውን ሀብት ተጠቅሞ የሥራ እድል ፈጠራን ለማሳካት የተያዘውእቅድ ህዝብን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በመሆናቸው እንዲጠናከሩ ጠይቀው፣ ለዕቀዱ ስኬታማነት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
በተለይ የመንገድ፣ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማትና ማኅበራዊ ተቋማትን ለማስፋፋት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የህዝቡ የልማት ጥያቄዎችን የሚመልሱ በመሆናቸው ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
መድረኩን የመሩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ለመደመር መንግስት ሰው ተኮር የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ስኬታማነት የሕዝቡ ቅንጅታዊ ሥራ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
መንግስት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በፍትሃዊነት ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ህዝቡ የቆየ የአብሮነት፣ የሰላምና የልማት እሴቶቹን ይበልጥ በማጎልበት በመደመር መንግሥት የተያዙ የልማት ትልሞች እንዲሳኩ የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የክልሉና የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም ከተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።