የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካ ዋንጫ ውጪ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካ ዋንጫ ውጪ ሆነ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ማጣሪያ ከሩዋንዳ አቻው ጋር ባደረገው የደረጃ ጨዋታ 2 ለ 1 ተሸንፏል።
በኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሄይለን ጄይደን ሼማ እና ኒዲዜዬ ኢሳቅ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
አክረም አብዱሰላም የኢትዮጵያን ብቸኛ ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሁለተኛ አጋማሽ ግቦችን ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ውጤቱን ተከትሎ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ አልቻለም። በማጣሪያ ውድድሩ አራተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
የሩዋንዳ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሶስተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ለአፍሪካ ዋንጫ አልፏል።
ዩጋንዳ እና ሶማሊያ ሌሎች ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፉ ሀገራት ናቸው።
ቡድኖቹ በአሁኑ ሰዓት የፍጻሜ ጨዋታቸውን እያደረጉ ነው።
ሶስቱ ሀገራት የሴካፋ ዞንን ወክለው እ.አ.አ በ2027 በሚካሄደው 17ኛው ከ17 ዓመት የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ይሳተፋሉ።
በሞሮኮ አስተናጋጅነነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ራሷን ሞሮኮ ጨምሮ 16 ሀገራት ይሳተፋሉ።