ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለዲጂታል ክህሎት ልማት ጠንካራ መሠረት ጥላለች-እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2019 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና ለዲጂታል ክህሎት ልማት ጠንካራ መሠረት መጣሏን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።

የ2026 የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በታይላንድ ባንኮክ ተካሄዷል።

ከዓመታዊው ስብሰባ ጎን ለጎን ዓለም ባንክ ያዘጋጀው የሰው ሀብት ሚኒስትሮች የከፍተኛ ውይይት መድረክ ተካሂዷል።


 

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና ለዲጂታል ክህሎት ልማት የጣለችውን ጠንካራ መሠረት አንስተዋል።

ብሔራዊ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ፖሊሲን፣የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን፣ የአምስት ሚሊዮን ኮደሮች ኢኒሼቲቭን እና የመደመር ኤአይ ዩኒቨርሲቲን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ ሥራ ላይ የዋሉትን የኤአይ አሰልጣኝ (AI Coach) እና የኤአይ አስተማሪ (AI Tutor) ፕሮግራሞችን አንስተዋል።

ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ውስጥ ስደተኞችና ተቀባይ ማህበረሰቦችን ጨምሮ ለወጣቶች የሚሆን በኤአይ የሚታገዝና የጾታ እኩልነትን ያቀናጀ ክህሎቶች ለሥራ እድል (Skills-for-Jobs) የትብብር ማዕቀፍ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።


 

የክህሎት ልማት የመንግሥት፣የአሰሪዎች እና የስልጠና ተቋማት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰው የስልጠናዎች ስኬት መመዘን ያለበት ሰልጣኞች ለገበያው የሚመጥን ተዛማጅ ክህሎት አግኝተው በቋሚነት ወደ ስራ በመሰማራተቸው እንጂ ስልጠና የወሰዱ ሰዎችን ብዛት በመቁጠር ሊሆን እንደማይገባ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ለክህሎት ልማት የሚሰበሰበው የግል ካፒታል በግልጽ የተቀመጡ የሕዝብ የቅድሚያ ፍላጎቶችን፣የጥራት ደረጃዎችን እና የፍትሃዊ ተደራሽነት መርሆዎችን መሠረት ያደረገ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ይህ ከፍተኛ የውይይት መድረክ በዓለም ባንክ የሰው ሀብት ፕሮጀክት (Human Capital Project) አስተባባሪነት የተዘጋጀ ሲሆን ሁነቱ በሰው ሀብት ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ለማድረግ ቁርጠኝነት ያላቸው ሀገራት የፖሊሲ አውጪዎች መድረክ ነው።

ኢትዮጵያ መድረኩ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ንቁ ተሳታፊ እና የመሪነት ሚና ስትጫወት የቆየች ሀገር መሆኗ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም