በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጥራትና ፍጥነት እንዲጠናቀቁ ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጥራትና ፍጥነት እንዲጠናቀቁ ይሰራል
ቦንጋ ፤ ጥቅምት 9/2019 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጥራትና ፍጥነት እንዲጠናቀቁ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ፍቅሬ አማን ገለፁ።
በርዕሰ መስተዳድሩ የተመራ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በቦንጋ ከተማ በግንባታ ላይ የሚገኙ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ምልከታው የፕሮጀክቶቹን የግንባታ ሂደት በመፈተሽ፣ የአፈጻጸም ማነቆዎችን በመለየትና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ፕሮጀክቶቹን ለሕዝብ አገልግሎት ማብቃት ላይ ያተኮረ እንደሆነም ተመላክቷል።
በቦንጋ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤትና የክልል ተቋማት የቢሮ ሕንፃ፣ የቦንጋ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የኮሪደር ልማት ስራ እና የህዝብ ትራንስፖርት መናኸሪያ ደግሞ ከተጎበኙት ፕሮጀክቶች መካከል ናቸው።
በጉብኝቱ ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን እንደገለፁት፤ በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቁ በትኩረት ይሰራል።
ግንባታውን የሚያከናውኑ ተቋራጮችም በቂ የሰው ሀይል በመመደብና ስራቸውን በጥራት በማከናወን በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በተለይም የቦንጋ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ የሕዝብ የመልካም አስተዳድር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ግንባታውን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ስራ ለማስጀመር ከሚመለከተው አካል ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
በቦንጋ ከተማ የኮሪደር ልማት ስራም የኮሪደር ልማቱ እሳቤዎችን መሰረት በማድረግ ፣ የመዝናኛ ፓርክና የሕፃናት መጫወቻዎችን አካቶ በጥራትና በተደራጀ መልኩ ይሰራል ብለዋል።
ምቹና ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እየተገነባ የሚገኘዉ የቦንጋ የሕዝብ መናኸሪያም የስነአካላዊ ስራዉ 86 ነጥብ 5 በመቶ ላይ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን ቀሪ ስራዎችን የማጠናቀቅ ስራ በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ በተቀመጠላቸው ጊዜና ጥራት በፍጥነት እንዲከናወኑ በየደረጃዉ አስፈላጊዉ ድጋፍና የቅርብ ክትትል እንደሚደረግም ርእሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡