የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አማራጭ መሰረተ ልማት የዜጎችን ተጠቃሚነት እያጎለበተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አማራጭ መሰረተ ልማት የዜጎችን ተጠቃሚነት እያጎለበተ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አማራጭ መሰረተ ልማት የዜጎችን ተጠቃሚነት እያጎለበተ መሆኑን በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሪፊኬሽንና ኢነርጂ መረጃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ዳቢ ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
ኢትዮጵያ በውሃ፣ በንፋስ፣ በፀሐይ፣ ጂኦተርማልና በባዮጋዝ ለዜጎች ኃይል አቅርቦት በማሟላት አፍሪካዊት የታዳሽ ኃይል ልማት መሪ የሚያደርጋትን አቅም እያጎለበተች ትገኛለች ።
የኢትዮጵያ ሰፊ የታዳሽ ኃይል መሰረተ ልማት ዝርጋታም የሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገር ለጎረቤት ሀገራት የሚደረገውን የኃይል ኤክስፖርት ለማሳደግ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው።
ይህም የመደመር መንግሥት የኃይል አማራጭ መሰረተ ልማት በማስፋት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን የሚያሳልጥ የኃይል አቅርቦት አቅም እየገነባ እንደሚገኝ ያመላክታል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሪፊኬሽንና ኢነርጂ መረጃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ዳቢ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በሁሉም አማራጮች ታዳሽ ኃይልን የማመንጨት ከፍተኛ አቅም አላት።
በዚህም የኢትዮጵያን በውሃ፣ ንፋስ፣ ፀሐይና በጂኦተርማል ኃይል የማመንጫ ጸጋዎችን በመጠቀም ለዜጎች የኃይል አቅርቦት ፍላጎት ምላሽ እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የታዳሽ ኃይል የመሰረተ ልማት አቅርቦት በማስፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረትም የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅትም በዜጎች ትብብር የተገነባው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም 10 ሺህ ሜጋ ዋት ማድረስ እንዳስቻለ ገልጸዋል።
የመደመር መንግሥት የኃይል አቅርቦት መሰረተ ልማት ግንባታና ተደራሽነትም የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በሀገር ዕድገት ላይ ጉልህ ሚና እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።
ከዋናው የኃይል ቋት በርቀት የሚገኙ አርሶና አርብቶ አደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም የፀሐይና የባዮጋዝ መሰረተ ልማት ተደራሽነት ትኩረት እንደተሰጠው አስረድተዋል።
ይህም አርሶና አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ በቴክኖሎጂ የታገዘ የውሃ ፓምፕ በመጠቀም የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ የግብርና ሥራ የሚያሳልጡበትን ዕድል እየፈጠረ ነው ብለዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብርም የኃይል ማመንጫ ግድቦችን የውሃ ደኅንነት አስተማማኝነት በማጎልበትና ደለልን በመከላከል ስትራቴጂክ ፋይዳ እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይ በዓባይ፣ በጊቤና ሌሎች የኢትዮጵያ ወንዞች ተፋሰስ በአረንጓዴ ዐሻራ የሚከናወኑ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች ለኃይል ማመንጫ ግድቦች ከፍተኛ ጠቀሜታ እያበረከቱ እንደሚገኝ አብራርተዋል።