ቀጥታ፡

ጣና ፎረም ኢትዮጵያ ለአህጉራዊ አጋርነት ያላትን ቁርጠኝነት የምታሳይበት መድረክ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2019 (ኢዜአ)፦ጣና ፎረም በአፍሪካ ወሳኝ የሰላምና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ግልጽ ውይይት የሚደረግበትና ኢትዮጵያ ለአህጉራዊ አጋርነት ያላትን ቁርጠኝነት የምታሳይበት መድረክ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ገለጹ።

ኢትዮጵያ የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማዕከል በማድረግ የሚዘጋጀውን የጣና ፎረም ለ15 ዓመታት በስኬት አስተናግዳለች።

12ኛው የጣና ፎረም "አፍሪካን ወደ ሰላም የሚወስዱ መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የቀጣናዊ ፖለቲካዊ ሽግግር" በሚል መሪ ሀሳብ የፊታችን አርብ በባህር ዳር መካሄድ ይጀምራል።


 

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የጣና ፎረም መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ሲቪክ ማህበራትና ምሁራን ዕውቀትን መሰረት አድርገው በነፃነት የሚወያዩበት መድረክ ነው።

በዓለም ላይ ሀገራት በችግሮቻቸው ላይ የሚወያዩበት ዘርፈ ብዙ መድረክ ቢኖራቸውም፤ አፍሪካ ለዚህ አልታደለችም ነበር ብለዋል።

ይሁን እንጂ ጣና ፎረም የአፍሪካ መሪዎች ከተለመደው የፖለቲካ መድረክ በተለየ መንገድ ቁጭ ብለው የሚወያዩበትን ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል። 

ጣና ፎረም በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ላይ ሀሳቦችን በነፃነት ማንሸራሸር ማስቻሉን ገልጸው፤ በአህጉሪቱ ወሳኝ የሰላምና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ የሚመክር የንግግር መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በፎረሙ አፍሪካ የዓለምን እንቅስቃሴ፣ የራሷን ችግሮች፣ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች የምታይበት መነፅር በአግባቡ መፈተሽ፣ ማየትና መቅርጽ የሚያስችል ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።

የአፍሪካን አጀንዳዎች ለዓለም አስተዋውቋል ያሉት አምባሳደር ዘሪሁን፤ አፍሪካ አሁን ያለችበትንና በቀጣይ የምትፈልገውን ማሳየቱንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከጅምሩ የጣና ፎረም ባለቤት ሆና መቀጠሏን ገልጸው፤ ከዚህ አህጉራዊ ጠቀሜታ ያለው ፎረም አህጉራዊ መሪነቷንና አጋርነቷን  አሳይታበታለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም