ቀጥታ፡

በምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላምን የማጽናትና ልማትን የማፋጠን ተግባራት ይጠናከራሉ

ገንዳውኃ፤ ጥቅምት 9/2019 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላምን በዘላቂነት ለማጽናትና ልማትን የማፋጠን ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የዞኑ አስተዳደር ገለጸ። 

በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ዮሐንስ ከተማ በወቅታዊ  ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሕዝባዊ ውይይት ተካሄደ።


 

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሆናለም አሻግሬ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፣ ሰላምን በዘላቂነት የማጽናትና ልማትን የማፋጠን ተግባራት ይጠናከራሉ።

በዚህም አካባቢውን የኢንቨስትመንት፣ የኢንዱስትሪና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ መላው የአካባቢው ህብረተሰብ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደረሰ አዱኛ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ወንጀሎችን ለመከላከል የተደረገው ጥረት ውጤት አስመዝግቧል።

ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ በመንግስት ብቻ ስኬታማ አይሆንም ያሉት ኃላፊው፣ ህብረተሰቡ የወንጀል ድርጊቶችን በማውገዝና በመታገል ያሳየውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።

ሻለቃ ነጋሲ ገብረ-ኤልያስ እንዳሉት፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከህዝቡ ጋር በቅንጅት በመስራት በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም ማስፈኑን ጠቁመዋል።

ህዝቡም ለሰራዊቱ አስተማማኝ ደጀን በመሆን በህግ ማስከበር ሥራው ኃላፊነቱን በመወጣቱ ምስጋና አቅርበዋል።


 

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ሸክ አህመድ እንድሪስ በበኩላቸው፣ መንግስት ሰላምን ለማጽናት በሚያደርገው ጥረት ከመንግስት ጎን በመቆም እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢያቸው ሰላምን በማጽናት ልማትን ለማረጋገጥ ህዝቡን በማስተማር በንቃት መሳተፋቸውን ያነሱት ደግሞ ቄስ ወልደ ሰንበት ማሞ ናቸው።

በመድረኩ ሰላምን ለማጽናት የሚያግዝ ወጣቶችን፣ የሀይማኖት አባቶችንና የአገር ሽማግሌዎችን ያካተተ የሰላም ካውንስል መቋቋሙም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም