በሰሜን ሸዋ ዞን በበጋ መስኖ ከ76 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ማልማት ተጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ሸዋ ዞን በበጋ መስኖ ከ76 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ማልማት ተጀምሯል
ደብረ ብርሃን ፤ ጥቅምት 9/2019 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በበጋ መስኖ ከ76 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የመስኖ አጠቃቀም ባለሙያ አቶ የሺጌታ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የበጋ መስኖ ልማት አርሶ አደሩ በምግብ ራሱን ከመቻል ባለፈ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት እያስቻለ ነው።
በያዝነው የበጋ ወራትም የተለያዩ የውሀ አማራጮችን በመጠቀም 76 ሺህ 557 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎችና አትክልትና ፍራፍሬ ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
በበጋ መስኖ ከሚለማው መሬት ውስጥ 60 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በስንዴ ዘር የሚሸፈን ሲሆን ቀሪው በሌሎች ሰብሎችና አትክልትና ፍራፍሬ እንደሚለማ ተናግረዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግ 17 ሺህ 254 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያና 35 ሺህ 448 ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መቅረቡን አመልክተዋል።
በዞኑ በዘንድሮ በጋ በመስኖ ከሚለማው አጠቃላይ መሬት 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።
በዞኑ እንሳሮ ወረዳ ነዋሪ አቶ መዘምር ደሳለኝ በአካባቢያቸው የሚገኘውን የሮቢ ወንዝን በመጥለፍ ቀይ ሽንኩርት፣ ካሮት፣ ቀይ ስር፣ ድንችና ቲማቲም ማልማት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በመስኖ ካለሙት ምርት ሽያጭ ባገኙት ገቢ መኖሪያ ቤቶች በመገንባት አከራይተው እየተጠቀሙ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት ከዘርፉ የሚያገኙትን ጥቅም ለማስፋት አቅደው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል።
የኤፍራታና ግድም ወረዳ ነዋሪ አቶ የሱፍ ይማም በበኩላቸው፤ ግማሽ ሄክታር መሬታቸው ላይ ቀይ ሽንኩርትና በርበሬ እያለሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል።