ቀጥታ፡

የህዝቡን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ በትጋት እንሰራለን 

ወልቂጤ ፤ ጥቅምት 9/2019 (ኢዜአ)፦ በተደመረ አቅም የህዝባችንን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ በትጋት እንሰራለን ሲሉ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል  ርዕሰ መስተዳድር  የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ተናገሩ።

"በመደመር መንግስት፣ የህዝብ ድምፅ፣ የጋራ ተሳትፎ፣ የጋራ ልማት!" በሚል መሪ ሀሳብ  የህዝብ ውይይት መድረክ ከቀቤና ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፣ የመደመር መንግስት የገባውን ቃል ወደ ተግባር በመቀየር የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባሩ ነው፡፡

የህዝቡን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ በጊዜ የለኝም መንፈስ በትጋት እና በቅንነት እንሰራለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ብቁ እንዲሆኑ የመንግስት እና የህዝብ አቅም ተሳትፎ በማጎልበት እንደሚሰራም ተናግረዋል።


 

የክልሉን ህዝብ አብሮነት በማጠናከር ልማትን የማፋጠን ሥራ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ተግባር መሆኑን ያነሱት ርዕስ መስተዳድሩ፤ የቀቤና ህዝብ ሰላምና አንድነትን የሚያፀናበት፤ በጋራ ለመለወጥ የሚያስችልና ዘመናትን የዘለቀ እሴት ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሃመድአሚን በደዊ እንዳሉት ፤ በልዩ ወረዳው ያለውን የተፈጥሮ ጸጋ፣ ልምድና የህዝብን የጋራ እሴቶች በማቀናጀት በተደመረ አቅም የመጣው ተጨባጭ ለውጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል።


 

የህዝቡን የዘመናት ጥያቄ የመደመር መንግስት በመመለሱ ህዝቡ ፊቱን ወደ ልማት እንዲመልስ ማድረጉን ተናግረዋል።

በዚህም በህብረተሰቡ በራሱ ተነሳሽነት 657 ሚሊዮን ብር በማውጣት ሆስፒታል እየተገነባ መሆኑን የተናገሩት አቶ መሀመድአሚን፤ በተቀናጀ የልማት አቅም የሚተገበሩ የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።

በውይይት መርሃ ግብሩ ላይ የክልል፣ የልዩ ወረዳው አስተዳደር የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም