ቀጥታ፡

የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ወደ ሥራ መግባት የአካባቢውን ቱሪዝም ከማነቃቃት ባለፈ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ አድርጎናል

ጎንደር ፤ ጥቅምት 9/2019 (ኢዜአ)፦ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ወደ ሥራ መግባት የአካባቢውን ቱሪዝም ከማነቃቃት ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ አድርጎናል ሲሉ  የአካባቢው ነዋሪዎች ገለፁ። 

የጎርጎራ ከተማ በታሪካዊ ገዳማቷ፣ በባሕር ትራንስፖርት መነሻነቷ እና በጀልባ ግንባታ ቀደምትነቷ የምትታወቅ ውብ የቱሪስት መዳረሻ ናት። 

ከተማዋ ከቀድሞ ዘመናት ጀምሮ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰትና የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባት የነበረች ቢሆንም፣ በሂደት እየቀዛቀዘ መጥቶ የቆየው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተጠቃሚነቷን አዳክሞት ቆይቷል። 


 

ይሁን እንጂ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት መገንባትና በወደቡ በኩል የሚከናወኑ የጀልባ ማምረትና የትራንስፖርት ሥራዎች እንደ አዲስ መነቃቃትን በመፍጠር የአካባቢውን የተፈጥሮ ጸጋዎች ለዓለም ማስተዋወቅ አስችለዋል።

የበርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች የመዝናኛ ማዕከል የነበረችውን የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት መገንባት እንደ አዲስ የአካባቢውን ጸጋ እንዲገለጥ ያስቻለ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ገልጸዋል።


 

የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ ደርጉ ዘለቀ እንደገለጹት፣ ከተማዋ ቀደም ሲል የጎብኚዎች ማረፊያና የጀልባ መገጣጠሚያ ሥራዎች የሚከናወኑባት ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ይታይባት የነበረች ናት።

አዲሱ የሪዞርት ፕሮጀክት ከግንባታው ጀምሮ በርካታ ሠራተኞችን በመቅጠር ለአካባቢው ማህበረሰብ ሰፊ የሥራ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

ሪዞርቱ ከአካባቢው ተፈጥሯዊ እሴትና ሀብት ጋር ተጣጥሞ መገንባቱም የተለየ ውበት በመፍጠር ቱሪስቶችን በእጅጉ የሚስብ ሆኗል ብለዋል።

"በባሕር ዳርና በጎርጎራ መካከል የባህር ትራንስፖርት ንቅናቄና የቱሪዝም ፍሰት በመጨመሩ ለአካባቢው ማህበረሰብ ሰፊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን አስገኝቷል" ያሉት ደግሞ ሐጂ ዛይደ ካሴ ናቸው።


 

እንደ ሐጂ ዛይደ ገለጻ፣ ጎርጎራ ከደርግ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ሥራ ላይ የነበረ ቢሆንም በሂደት እየተቀዛቀዘ መጥቶ ለጎብኚዎች እምብዛም አገልግሎት እየሰጠ አልነበረም ብለዋል።

የሪዞርቱ መገንባት የእንግዶችን ቆይታ ከማራዘምና ባሕር ዳርን ከጎንደርና ደባርቅ ከተማ ጋር በማገናኘት ለአካባቢው ልዩ የኢኮኖሚ አብዮት እየፈጠረ ነው ብለዋል።

ሌላኛዋ የአካባቢው ነዋሪ ወይዘሪት አዜብ ደርበው በበኩሏ፣ ጎርጎራ ቀደም ሲል በቱሪስት መዳረሻነቷ እና በወደብ ከተማነቷ የምትታወቅ ነበረች ብላለች።


 

ከጎንደር እስከ ባሕር ዳር ያሉ አካባቢዎችን በማገናኘት ሰርግና ሌሎች ዝግጅቶች እንዲሁም በጀልባ ላይ የንግድ ልውውጦች ይካሄዱባት እንደነበር አውስታለች።

አሁን ላይ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ወደ ሥራ መግባቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝምና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንደ አዲስ መነቃቃት ጀምሯል ብላለች።

የአካባቢው ማኅበረሰብም ለሪዞርቱ የምግብ ግብዓት ከማቅረብ ጀምሮ በሌሎች የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ተጠቃሚነቱን እያሳደገ መሆኑን ገልጻለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም