ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ የዘር ብዜት ስራ እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ የዘር ብዜት ስራ እያከናወነ ነው
ሐረማያ ፤ ጥቅምት 9/2019 (ኢዜአ)፦ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ የዘር ብዜት ስራ እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።
የዘር ብዜት ስራው ምርጥ ዘሮችን ለአርሶ አደሮች ለማዳረስ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተመላክቷል።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ፋሲሊቲ የሰብልና እንስሳት ልማት ቡድን አስተባባሪ ብርቱኳን ይማም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማርና ምርምር ስራው በተጓዷኝ የዘር ብዜት ስራ እያከናወነ ነው።
ዩኒቨርሲቲው የዘር ብዜቱን እያከናወነ የሚገኘው በዋናው ግቢ፣ በባቢሌ፣ በኩርፋ ጨሌ፣ በፈዲስ፣ በግራዋ ሂርና፣ ድሬዳዋን ጨምሮ በ14 የምርምር ጣቢያዎች መሆኑን ተናግረዋል።
የዘር ብዜት ስራው የሚከናወነው በቦሎቄ፣ በስንዴ፣ በአተር፣ በለውዝ፣ በባቄላና በሌሎች የሰብል አይነቶች እንዲሁም በድንች ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ምርጥ ዘሮቹ የዝናብ እጥረትንና በሽታን ተቋቁመው የተሻለ ምርት የሚሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የኢንተርፕራይዝ ልማት የግብርና መካናይዜሽን አስተባባሪ አቶ ታደሰ አዱኛ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው የምርጥ ዘር እጥረት እንዳይከሰት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በምርምር የተሻሻሉ የሰብል አይነቶች ላይ በማተኮር የዘር ብዜት ስራውን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት 'ቡቡ' እና 'ጉደኔ' የተሰኙ የድንች ዝርያዎችን በማባዛት 2ሺ ኩንታል ዘር በአካባቢው ለሚገኙ አርሶ አደሮችና ለሌሎች ተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ማሰራጨቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህርና የእንስሳት ፋርም አስተባባሪ ጉታ ኩምሳ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው እንስሳት ሀብት ልማትን ለማዘመንና ምርታማነት ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የእንስሳት እርባታ ማዕከል በቀን እስከ 30 ሊትር ወተት የሚሰጡ የከብቶች ዝርያን የማሻሻል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሰው ሰራሽ ስነ ዘዴ በመጠቀም ዝርያቸው የተሻሻሉ ከብቶችን ለአካባቢው ማህበረሰብና ለሌሎች ተቋማት በማቅረብ የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በዋናው ግቢ በሚያካሂደው የዘር ብዜት ስራ ላይ የተሳተፉት የአካባቢው ነዋሪ ወይዘሮ ጀሚላ ኡመር እንደገለጹት ዘንድሮ የዝናብ እጥረት ቢያጋጥምም መስኖን በመጠቀም የዘር ብዜት ስራ ተከናውኗል።
የሚሰበሰበው ምርት በዝናብ እጥረት ለሚያጋጥም የምርት እጥረት የማካካሻ ዘር አቅርቦት እንደሚያግዝም አመልክተዋል።