ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ሶስተኛ አላፊ ሀገር ለመሆን ከሩዋንዳ ጋር ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ማጣሪያ ከሩዋንዳ አቻው ጋር የደረጃ ጨዋታውን ዛሬ ያከናውናል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ በሩዋንዳ ኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም ይካሄዳል።

በአሜሪካዊው አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን  በግማሽ ፍጻሜው በዩጋንዳ 4 ለ 0 መሸነፉን ተከትሎ ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ የመጀመሪያ እድሉን ሳይጠቀም ቀርቷል።

ቡድኑ ዛሬ ከሩዋንዳ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ካሸነፈ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ያረጋግጣል።

የውድድሩ አዘጋጅ ሩዋንዳ በግማሽ ፍጻሜው በሶማሊያ  በመለያ ምት  መሸነፏ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ከሩዋንዳ ጋር ለሶስተኛ ደረጃ እንዲሁም ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከሚያደርገው ወሳኝ ጨዋታ አስቀድሞ ትናንት በኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም ልምምዱን ማከናወኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ብሔራዊ ቡድኑ እ.አ.አ በ2026 በሞሮኮ በተካሄደው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፉ የሚታወስ ነው።

የማጣሪያው የፍጻሜ ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ላይ በዩጋንዳ እና ሶማሊያ መካከል ይደረጋል።

ሁለቱ ሀገራት ለፍጻሜ ማለፋቸውን ተከትሎ እ.አ.አ በ2027 በሞሮኮ ለሚካሄደው 17ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፋቸውን አረጋግጠዋል።

በሩዋንዳ  አስተናጋጅነት ከመስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም አንስቶ ሲካሄድ የቆየው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ማጣሪያ ዛሬ ይጠናቀቃል።

በውድድሩ ላይ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ የሚወጡ ሀገራት የሴካፋ ዞንን ወክለው እ.አ.አ በ2027 በሞሮኮ አስተናጋጅነት በሚካሄደው 17ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ላይ እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መረጃ ያመለክታል።

በሞሮኮ አስተናጋጅነነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ራሷን ሞሮኮን ጨምሮ 16 ሀገራት ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም