በድሬዳዋ የትምህርት ጥራትን የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው በጀትና ጥራት ለማጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ የትምህርት ጥራትን የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው በጀትና ጥራት ለማጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቷል
ድሬዳዋ፤ ጥቅምት 8/2019(ኢዜአ)፡-በድሬዳዋ አስተዳደር የትምህርት ጥራትን የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው በጀትና በጥራት ለማጠናቀቅ ትኩረት መሰጠቱን የአስተዳደሩ ከንቲባ አብዱላሂ አደን ገለጹ።
ከንቲባው በድሬዳዋ ገጠርና ከተማ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር እያስገነባቸው የሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ፣ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ እና የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታዎችን ሂደት ተመልክተዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አብዱላሂ አደን በወቅቱ እንደተናገሩት፤ አስተዳደሩ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ቅንጅታዊ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ነው።
በድሬዳዋ በገጠርና በከተማ የተተገበሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው በጀት፣ ጊዜና ጥራት ተጠናቀው የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ አስተዳደሩ ክትትልና ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠሉን አውስተዋል።
የዛሬው ጉብኝትም የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በድሬደዋ በአጋር አካላት የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናቀቅ በሚደረገው ጥረት አስተዳደሩ የድርሻውን ለመወጣት ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በግብአት አቅርቦትና በሰው ሀይል ልማት ላይ ከሚሰራው ሥራ ጎን ለጎን የምገባ ማዕከላት ላይ በትኩረት መሰራቱንም አንስተዋል።
በከተማ እና ገጠር የትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ መርሃግብር ስኬታማ እንዲሆን የተጀመሩ የተማሪዎች የምገባ ማዕከላት በፍጥነት ተጠናቀው በሙሉ አቅም ወደ አገልግሎት እንዲገቡ መሰራቱን አስረድተዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ በበኩላቸው ሕፃናት በምግብ ዕጥረት ከትምህርት ገበታ እንዳይለዩ በተያዘው ዓመት በተማሪዎች ምገባ ላይ በርብርብ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል ።
የምገባ መርሀ ግብሩም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥን ለመቀነስ የማይተካ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል።
በፌደራል መንግስት የተጀመሩ የትምህርት ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ በጋራ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ሱልጣን እስታወቀዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ለትምህርት ቤት ምገባ መርሀግብር የምገባ ማዕከላዊ ማብሰያ ግንባታና በ18 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የፍራፍሬ ልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በትምህርት ፕሮጀክቶቹ ጉብኝት ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር የካቢኔ አባላት የተሳተፉ ሲሆን፣ ከጉብኝቱ በተጨማሪ በባለሃብት ለሚገነባው የአረጋውያንን እና የሕፃናት መንከባከቢያ ማዕከልም በከንቲባው የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።