ቀጥታ፡

የሰመራ ከተማ የኮሪደር ልማት ለነዋሪዎች ምቹ የመዝናኛና የማኅበራዊ መስተጋብር ማዕከል ሆኗል- የሰመራ ከተማ ወጣቶች

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 8/2019 (ኢዜአ)፦የሰመራ ከተማ የኮሪደር ልማት ለነዋሪዎች ምቹ የመዝናኛና የማኅበራዊ መስተጋብር ማዕከል መሆን መቻሉን በአፋር ክልል የሰመራ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።

በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለኮሪደር ልማት የተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ከተሞችን ዘመናዊ፣ ፅዱ እና ለዜጎች ምቹ የመኖሪያና የሥራ አካባቢ አድርጎ የመቀየር ትልቅ አቅም ፈጥሯል።

ይህ ሰፊ የመሠረተ ልማት ማሻሻያ ለዜጎች ምቹ የእግር መንገድን፣ የመዝናኛ ስፍራዎችንና የትራፊክ ፍሰትን ከማሳለጡ ባሻገር፣ የሀገሪቷን የቱሪዝም መስህብነት በማሳደግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

በተጨማሪም የኮሪደር ልማቱ አዳዲስ የንግድ እድሎችን በመክፈትና ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከር ለሀገሪቷ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው።

ይህ ውጤታማ ተግባር ከአዲስ አበባ ባሻገር በተለያዩ የክልል ከተሞች ተጠናክሮ የመቀጠሉ አወንታዊ እንቅስቃሴ የክልሎችን ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ እየቀየረው ይገኛል።


 

ኢዜአ  ያነጋገሯቸው የሰመራ ከተማ ወጣቶች እንደገለጹት፣ በከተማው የተካሄደው የኮሪደር ልማት የከተማውን ገጽታ በማሻሻል ለኑሮ፣ ለስራ እና ለማህበራዊ ትስስር የተመቸች አድርጓታል።

የሰመራ ከተማ ነዋሪ ወጣት ተፈሪ ማቴዎስ፣ የኮሪደር መሠረተ ልማት ሥራዎች ከመጀመራቸው በፊት ለወጣቶችም ሆነ ለሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሆን የመዝናኛ ቦታዎች እጥረት እንደነበር አስታውሷል።

አሁን ግን በከተማዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ውብ ገጽታን ከማላበስ ባለፈ ከሥራ ውጪ ባለው ትርፍ ጊዜ አእምሮውን  ለማሳረፍ የሚሆን ምቹ አካባቢ መፈጠሩን ገልጿል።


 

ወጣት ሞሐመድ ደርሳ በበኩሉ፣ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን በመሠረተ ልማት ከማዘመን ባለፈ በነዋሪዎች መካከል ያለውን ማኅበራዊ ትስስርና መስተጋብር የሚያጠናክር መሆኑን ተናግሯል።

የልማት ሥራው ወጣቶች የስፖርት እንቅስቃሴ የሚያደርጉባቸውን ምቹ ሁኔታዎች በመፍጠር ንቁና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን እንዲከተሉ እንደሚያግዝም ገልጿል።

የኮሪደር ልማቱ ነዋሪዎች በቀንም ሆነ በሌሊት ያለ ስጋት በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የገለጸው ደግሞ ወጣት አብደላ ሙሳ ነው።


 

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወጣት ፋጢማ መሐመድ፣ የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን የመስተንግዶ አቅም ከማሳደግ ባለፈ የቱሪዝም ዘርፉ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጻለች።


 

እንደ ኤርታሌና ዳሎል ያሉ የአፋር ክልል የቱሪዝም መዳረሻዎች በርካታ ጎብኚዎችን በመሳብ ለክልሉና ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሚሆን ጠቁማለች። 

ስለሆነም የክልሉን የቱሪዝም ሀብት በስፋት ለማስተዋወቅና በዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀም የኮሪደር ልማት ሥራዎች በክልሉ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ወጣቶቹ ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ አያይዘውም ሀገራዊ የልማት ስራዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማከናወን ሰላም ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው፤ የአካባቢያችንን ሰላም መጠበቅ ይጠበቅብናል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም