ለመደመር መንግስት የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ስኬታማነት የበኩላችንን እንወጣለን-የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለመደመር መንግስት የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ስኬታማነት የበኩላችንን እንወጣለን-የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች
ወልቂጤ፤ ጥቅምት 8/2019 (ኢዜአ)፡-ለመደመር መንግስት የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ስኬታማነት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት በቀጣይ ለማከናወን በያዛቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅዶች ላይ ከዞኑ ነዋሪዎች ጋር ዛሬ በወልቂጤ ከተማ መክሯል።
በምክክር መድረኩ ላይ አስተያየት የሰጡ የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች፤ መንግስት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው የልማት ግቦች እንዲሳኩ ሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ሮዛ አግዛ በሕዝብ ድምጽ ምርጫ አሸንፎ የልማት እቅዶችን ከነደፈው መንግስት ጋር በቅንጅት በመስራት ለልማት ውጥኖች ስኬታማነት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
በተለይ ሰላምን በዘላቂነት ለማጽናትና ልማትን አጠናክሮ ለማስቀጠል የተቀየሱ እቅዶች ህዝብን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላሉ ብለዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ዳውድ ካሚል በበኩላቸው የመደመር መንግሥት የያዛቸው የልማት ግቦች ለትውልድ የምትመች ሀገርን ለመገንባት የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።
የልማት ግቦቹ የህብረተሰቡን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የአካባቢያቸውን ልማት እንደሚያፋጥኑ ገልጸው፣ በሥራ እድል ፈጠራም ወጣቱን ጨምሮ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ አንስተዋል።
መንግስት ለህዝብ የልማት ጥያቄዎች መፍትሄ ለመስጠት እየተከተለ ያለው የአመራር ጥበብን ያደነቁት ደግሞ አቶ ወልደሀዋሪያት ይርጋ የተባሉ ነዋሪ ናቸው።
በመደመር መንግሥት ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች በተለይ መንገድ፣ ውሃ፣ መብራትና ማኅበራዊ ተቋማትን ለማስፋፋት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ለህዝቡ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ያስችላሉ ብለዋል።
ለዚህም ከመንግስት ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ነው ያረጋገጡት።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) በክልሉ ለሚከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ስኬታማነት ሕዝቡ ቅንጅታዊ ሥራን ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የክልሉን ጸጋዎች በማልማት ለኢኮኖሚያዊና ለማህበራዊ ጥቅም ከማዋል በተጨማሪ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ የመንግስት አብይ ተግባር መሆኑንም አስታውቀዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም ከተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።