ቀጥታ፡

የሰቆጣ ዝናብ አጠር ግብርና ምርምር ማዕከል አዲስ የጤፍ ዝርያ ምርታማነታችንን የሚያሳድግ ነው

ሰቆጣ፤ ጥቅምት 8/2019 (ኢዜአ):-ከሰቆጣ ዝናብ አጠር ግብርና ምርምር ማዕከል የቀረበላቸው የተሻሻለ የጤፍ ዝርያ ምርታማነታቸውን እንደሚያሳድገው በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሰቆጣ ወረዳ አርሶ እደሮች ገለጹ።

በምርምር ማዕከሉ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ተጠቅመው ያለሙ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ ዛሬ ምልከታ ተደርጓል።


 

በሰቆጣ ወረዳ የቀበሌ 06 ነዋሪ አርሶ አደር ጌታወይ መኮንን እንደገለጹት፣ ከምርምር ማዕከሉ ያገኙትን "መና" የተባለ የጤፍ ዝርያ ለመጀመሪያ ጊዜ በግማሽ ሄክታር መሬታቸው ላይ አልምተዋል።

ዝርያው ዝናብ አጠር ለሆነው ለአካባቢያችን ተስማሚ ከመሆኑ በላይ በፍጥነት የሚደርስና ድርቅን ተቋቁሞ የተሻለ ምርት ለማግኘት የሚያስችለን ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የሰብሉ ቁመና በጥሩ ሁኔታ ላይ ስለሚገኝ ከግማሽ ሄክታር መሬታቸው ቀደም ሲል ያገኙት ከነበረው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።


 

ሌላው አርሶ አደር ያለው አገኝ በበኩላቸው "በምርምር ማዕከሉ የቀረበልኝን የተሻሻለ የጤፍ ዝርያ ተጠቅሜ በአንድ ሄክታር መሬቴ ላይ በኩታ ገጠም እያለማሁ ነው" ብለዋል።

የማዕከሉን የተሻሻለ የጤፍ ዝርያ ተጠቅመው ሲያለሙ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ጠቁመው፣ የተሻሻለው የጤፍ ዝርያ ከአካባቢው ዝርያ የበለጠ ምርት እንደሚሰጥ የፍሬ አያያዙ ያሳያል ብለዋል።

በሰቆጣ ወረዳ የሃሙሲት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አማረ አንበሳው በበኩላቸው በምርምር ማዕከሉ የቀረበላቸውን የተሻሻለ የጤፍ ዝርያ ተጠቅመው ከዘሩት አንድ ሄክታር መሬታቸው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።


 

የሰቆጣ ዝናብ አጠር ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አዳነ ባህሩ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ማዕከሉ የብሔረሰብ አስተዳድሩን ስነ-ምህዳር መሰረት ያደረጉ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን እያቀረበ ይገኛል።

በአነስተኛ ዝናብ ፈጥነው የሚደርሱ የጤፍ፣ የስንዴ፣ የማሽላና የዳጉሳ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ እያስፋፋ መሆኑን ገልጸው፣ በተሻሻለው የጤፍ ዝርያ በአርሶ አደሩ ማሳ በሄክታር እስከ 14 ኩንታል እየተገኘበት ነው ብለዋል።

የተሻሻሉ ዝርያዎቹ ለአካባቢው ሥነ ምህዳር ተስማሚ መሆናቸውን ገልጸው፣ ለበጋ ወራት የመስኖ ልማትም ተስማሚ የሆኑ የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ለማቅረብም እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።


 

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ በበኩላቸው፣ ምርምር ማዕከሉ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማቅረብ እያገዘ ይገኛል።

መምሪያው በማዕከሉ የሚወጡ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች ፈጥነው ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆኑ በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በአርሶ አደሮች ማሳ ምልከታ ላይ የግብርና አመራሮች፣ ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች መሳተፋቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም