በፍራፍሬ ልማት ዘርፍ በመሰማራት አርሶ አደሮች ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በፍራፍሬ ልማት ዘርፍ በመሰማራት አርሶ አደሮች ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ ነው
ደሴ፣ ጥቅምት 8/2019(ኢዜአ)፦ ከሰብል ልማቱ በተጨማሪ በፍራፍሬ ልማት ዘርፍ በመሰማራት ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ እንደሚገኙ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የዳዋጨፋ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።
የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ደዋጨፋ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማ ፍራፍሬ ልማት ጎብኝተዋል።
በወረዳው የገርቢ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር መሀመድ ሀሰን እንደተናገሩት፤ የአካባቢውን ለፍራፍሬ ልማት ምቹነት በመጠቀም በዘርፉ በመሰማራት ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ ይገኛሉ።
ቀደም ሲል ያለሙት የሙዝ ተክል አሁን ላይ ምርት መስጠት በመጀመሩ ለገበያ በማቅረብ ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ባለፈው ክረምት ድርቅን ተቋቁሞ በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጥ የሙዝ ችግኝ እንደተሰጣቸው የጠቆሙት አርሶ አደሩ፤ ተጨማሪ አንድ ሄክታር መሬት በኩታገጠም በማልማት እያገኙት ያለውን ጥቅም ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ሌላዋ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አንሻ ሁሴን በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል በቆሎ፣ ሽንኩርትና ቲማቲም ያለሙበት የነበረውን ግማሽ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በሙዝ በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሥራው ዘላቂ ተጠቃሚ ያደረጋቸው ከመሆኑም በላይ ለልጆቻቸው የሚተላለፍ ቋሚ ንብረት በመሆኑ መደሰታቸውንም ተናግረዋል።
"በፍራፍሬ ልማት በመሰማራታችን ከነቤተሰባችን የተሻለ ተጠቃሚ እየሆን ነው” ያሉት ደግሞ የተረፍ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር እንድሪስ አሊ ናቸው።
በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጀማል አሊ በበኩላቸው፤ ዞኑ ለፍራፍሬ ልማት ያለውን ምቹነት በመጠቀም የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።
አርሶ አደሩን በማደራጀት ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ብርቱካን፣ አቮካዶና ሌሎች ፍራፍሬዎችን በኩታገጠም በማልማት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ብቻ 520 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም ፍራፍሬ ማልማት መቻሉን ጠቁመው፣ ይህም ባጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው በበኩላቸው፤ ክልሉ ለፍራፍሬ ልማት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተቻለ ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት ቡናና አቮካዶን ጨምሮ ሌሎች የፍራፍሬ አይነቶችን በማምረት ከፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ጭምር ማቅረብ መቻሉን ለአብነት አንስተዋል።
የተገኘውን ጥቅም ለማስፋትም ባለፈው ዓመት ብቻ አርሶ አደሩን በማደራጀት 28 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም የፍራፍሬ ልማት ማልማት መቻሉን አንስተዋል።
ዘንድሮም 60 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ፍራፍሬ ለማልማት በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡና በሽታን የሚቋቋሙ ችግኞችን የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን በማንሳት።
በጉብኝቱ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።