በአማራ ክልል በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዜጎችን የልማት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዜጎችን የልማት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል
ባህር ዳር፤ ጥቅምት 8/2019(ኢዜአ)፡-በህብረተሰቡ ዘንድ ባህል እየሆነ በመጣው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዜጎችን የልማት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ ገለጹ።
በክልሉ የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማጠቃለያና የበጋው በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሀግብር መስጀመሪያ ክልላዊ መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ በመድረኩ እንደገለጹት በመንግስት ትኩረት የተሰጠው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በህብረተሰቡ ዘንድ ባህል እየሆነ መጥቷል።
በዚህም ባለፉት ዓመታት በጎ ፈቃደኛ ወገኖችን በማሳተፍና በማስተባበር ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፤ በተለይ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርናና አቅመ ደካማ ወገኖችን በመደገፍ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚከናወኑ ተግባራት የመንግስትን የልማት ክፍተት በመሸፈን ለክልላዊ እድገቱ የራሳቸውን አስተዋጾ ማድረጋቸውንም አረጋግጠዋል።
በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተገኘውን ተሞክሮ በመቀመር በተያዘው የበጋ ወራትም አጠናክሮ በማስቀጠል ከድህንት ለመውጣት በትኩረት መስራት እንደሚገባም አቶ ይርጋ አሳስብዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ በበኩላቸው እንዳሉት በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በክልሉ ከ10 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ ውጤታማ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።
በጎ ፈቃደኞች በጉልበታቸው እና ገንዘብ በማሰባሰብ ባከናወኗቸው የልማት ሥራዎች ከ15 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚመሆናቸውን አመልከተዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ ብርቱካን ገለጻ በ2018 የክረምት ወራት ከ29 ሺህ 860 በላይ የአዲስ ቤቶች ግንባታና የነባር ቤቶች እድሳት ሥራ በማከናወን ለአቅመ ደካማ ወገኖች ማስረከብ ተችሏል።
በመድረኩ ላይም የክልሉ መንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ ባለሙያዎች፣ በጎ ፈቃደኞች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች መታደማቸው ታውቋል።