የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ለቀጣናው ሰላምና ለጋራ እድገት ወሳኝ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ለቀጣናው ሰላምና ለጋራ እድገት ወሳኝ ሚና አለው
አዳማ፤ ጥቅምት 8/2019 (ኢዜአ) ፡-ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ለቀጣናው ሰላም፣ ለጋራ እድገትና ለኢኮኖሚያዊ ትስስር የጎላ ድርሻ እንዳለው የአዳማ ከተማ ወጣቶች ገለፁ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ህዝብ፣ ታላቅ ርእይ
ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ያለችና ግዙፍ የሕዝብ ቁጥር ያላት ሀገር በመሆኗ፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋን የሚመጥን አስተማማኝ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መናገራቸው ይታወሳል።
ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት፤ ሀገሪቱ በፍጥነት እያደገ ከመጣው የንግድ ፍላጎቷ አንጻር ወደ ዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች የሚያደርሱ አስተማማኝ የባሕር በር አማራጮች ሊኖሯት ይገባል።
ይህንን ሕጋዊና ፍትሐዊ የባሕር በር የማግኘት ግቧን ለማሳካት የምትከተለው መንገድ በውይይት፣ በዲፕሎማሲያዊና በጋራ ስምምነቶች ላይ የተመሠረተ፤ የቀጣናውን ሀገራት ጥቅም በሚያስጠብቅና የጋራ ዕድገትን በሚያረጋግጥ መልኩ በስምምነት ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗንም ገልጸዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ የባሕር በር አማራጮቿን ለማስፋት የምታደርገው ጥረት ዋና ዓላማ ከፍተኛ የሆነውን የትራንስፖርትና የንግድ ወጪ ለመቀነስ፣ ሀገራዊ የኢኮኖሚ አቅምን ለማጠናከር እና በቀጣናው ሀገራት መካከል ዘላቂነት ያለው የጋራ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፅንፆት ሰጥተውታል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዳማ ከተማ ወጣቶች እንዳሉት የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ለቀጣናው ሰላም እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ከፍተኛ ፋይዳ አለው።
በአዳማ ከተማ የኢሬቻ ወረዳ ነዋሪ ወጣት አብርሃም ሸመልስ በሰጠው አስተያየት የመደመር መንግሥት ለዓመታት ያልተመለሰውን የባህር በር የማግኘት ጥያቄ እልባት ለመስጠት እያደረገ ያለው ያላሳለሰ ጥረት የሚደነቅ ነው።
ሰፊ የህዝብ ቁጥር እንዳላት ሀገር ካለባህር በር ለመኖር አዳጋች እንደሚሆንባት ጠቅሶ፤ የመደመር መንግሥት የባሕር በር ለማግኘት የሚከተለው ሰላማዊ እና የሰጥቶ መቀበል መርህ የሚደገፍ ነው ብሏል።
ከዚህ አኳያ የባሕር በር ባለቤትነት የመላው ዜጋ የጋራ አጀንዳ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ነው ያለው።
እንደ ወጣቱ ገለፃ አሁን ላይ መንግስት እያራመደ ያለው የባህር በር የማግኘት የማያወላዳ አቋም በዓለም አቀፍ ደረጃ እያገኘ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ተቀባይነት ተስፋ ሰጪ መሆኑንተናግሯል።
ወጣት ቃልኪዳን ወርቁ በበኩሏ ከባህር በር ጋር ተያይዞ ሀገራችን ለዓመታት ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ ቆየታለች፤ ይህ ሁኔታ የሚቆጭና ሊቀለበስ የሚገባው ጉዳይ ነው ትላለች።
የባሕር በር አለመኖር በውጭ ምንዛሬ ላይ ከፍተኛ ጫና ከመፍጠሩም ባለፈ በአገር ዕድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝም ሁሉም በውል ሊገነዘብ ይገባል ብላለች።
በመሆኑም በሀገራችን ላይ እስካሁን የደረሰው በደል ሊያበቃ ያስፈልጋል ባይ ነች።
በቀጣይም የባህር በር ለማግኘት ሁሉም ዜጋ ሊረባረብ እንደሚገባ ጠቅሳ፤ ይህም የጎረቤት ሀገርን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ የእኛም ሉአላዊነት ተከብሮ ጥቅማችን መጠበቅ እንዳለበት አመላክታለች።
ይህ አገራዊና የህልውና ጥረት እንዲሳካ ታዲያ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት እና በቁርጠኝነት በመቆም ለመንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አክላለች።
ወጣት ሶሬቻ ቀበኔቻ በበኩሉ፤ የመደመር መንግሥት በአዲሱ የመንግስት ምስረታ ላይ የባህር በር ጉዳይን ዋና አጀንዳ አድርጎ ማቅረቡ እንደ አንድ ዜጋ ኩራት ይሰማኛል ይላል።
ሀገራችን ለዓመታት የባሕር በር ማጣት በኢኮኖሚ ላይ ያሳደረው ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም የሚለው ወጣቱ፤ ከዚሀ አንፃር ችግሩን በሰጥቶ መቀበል መርህ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቋጨት መንግሥት እየተከተለ ያለውን ስልት አዋጫ በመሆኑ በጽኑ እንደሚደግፈው ተናግሯል።
በተለይም ሀገራችን በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን የጂኦፖለቲካ ሚና ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የባሕር በር ባለቤት ልትሆን አንደሚገባ ገልፆ፤ ይህም ለቀጣናው ሰላም እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ፋይዳው ወደር እንደሌለው አስረድቷል።