የከተማዋን ነዋሪዎች በፍትሃዊነት የቤት አቅርቦት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የከተማዋን ነዋሪዎች በፍትሃዊነት የቤት አቅርቦት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 8/2019 (ኢዜአ)፦የከተማዋን ነዋሪዎች በተለያዩ አማራጮች በፍትሃዊነት የቤት አቅርቦት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአቃቂ ቃሊቲ የበጎነት የመኖሪያ ሕንፃ ምረቃ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት ለሀገር ባለውለታዎችና አቅመ ደካሞች ቤት አስረክበዋል።
ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ቀደም ሲል የአካባቢው ገጽታ ለኑሮ ምቹ ያልሆነና የነዋሪዎችን ክብር የማይመጥን እንደነበር ገልጸዋል።
የቀድሞዎቹ ያረጁና የወዳደቁ የቀበሌ ቤቶች አሁን ላይ ተለውጠው ዘመናዊ የመኖሪያ ሕንፃ ተገንብቶ፣ ንጹህ፣ ምቹና የሰውን ክብር በጠበቀ መልኩ መኖር የሚቻልበት አካባቢ መፈጠሩን አስረድተዋል።
ከንቲባዋ አክለውም መንግሥት የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ ምቹ የኑሮ አካባቢ ለመፍጠርና የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል ከሕብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች በንጹህ፣ ምቹና የሰውን ክብር በጠበቀ አካባቢ እንዲኖሩ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
በተለይም ነዋሪዎች በኪራይና በተለያዩ የቤት አቅርቦት አማራጮች በፍትሐዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግሥት እየሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሀንጋቱ መሐመድ በበኩላቸው፤ ክፍለ ከተማው ባለፉት ዓመታት በርካታ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የተከናወኑበት የከተማዋ የኢኮኖሚ ሞተር መሆኑን ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለት ለተጠቃሚዎች የተላለፈው ቤትም የመደመር መንግሥት እሳቤ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
የቤት ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አስር አለቃ ዳንኤል የዓለሙና አራርሳ ደስታ እንዳሉት፣ ለበርካታ ዓመታት የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ሀሩርና ቁር፣ ዳገትና ቁልቁለቱን ወጥተውና ወርደው ለሀገር ሰላም ዘብ ቆመዋል።
በዛሬው ዕለት ለሀገር ክብር መስዋዕትነት ለከፈሉ ባለውለታዎች ቤት በመሰጠቱ ታላቅ ክብርና ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የነበረው የአካባቢው ገጽታ የተጎሳቆለና ለኑሮ አመቺ እንዳልነበረ የገለጹት ወይዘሮ ምስራቅ ጎንፋና አልማዝ አበራ፣ ንጹህና ጽዱ የመኖሪያ አካባቢ በማግኘታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የቄራ አልማዝዬ ስፖርት ትምህርትና ሥልጠና ማዕከል መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ የአልማዝዬ ሜዳ የስፖርት አፍቃሪውን ፍላጎት መሠረት በማድረግ እንደገና ተገንብቷል።
የአልማዝዬ ሜዳ የቀድሞ ስመ ጥርና አንጋፋ ተጫዋቾችን ያፈራ መሆኑን አመልክተው፣ መጪውን ትውልድ ታሳቢ በማድረግ በአዲስ መልክ መገንባቱን ተናግረዋል።
የከተማው አስተዳደር በ2019 በጀት ዓመት ከ150 በላይ የስፖርት ሜዳዎችን ለመገንባት ማቀዱንና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የስፖርት መሠረተ ልማት ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።
ባለፉት ዓመታት በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ግንባታ መከናወኑንና በክፍለ ከተማው ብቻ ከ280 በላይ ተገንብቷል ያሉት ደግሞ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አህመድ ሃሰን ናቸው።